ፕሪምየር ሊግ | የ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ – ክፍል 2

አርባምንጭ ፣ ዓዲግራት እና አዲስ አበባ ላይ የሚደረጉ ሶስት የነገ ጨዋታዎች የተጋጣሚዎቹ የፕሪምየር ሊግ ቆይታ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል። እኛም በክፍል ሁለት ቅድመ ዳሰሳችን እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።

ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ አዳማ ከተማ

ዓዲግራት ላይ የሚደረገው ይህ ጨዋታ ሁለቱንም ቡድኖች ባሉበት ፉክክር ውስጥ መሻሻልን ሊያመጣላቸው ይችላል። ላለመውረድ በምደረገው ትግል ውስጥ የሚገኘው ወልዋልም ዓ.ዩ ግንቦት አጋማሽ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ነጥቦችን እየሰበሰበ ከወራጅ ቀጠናው ወጥቷል። ሆኖም ሙሉ ለሙሉ ከስጋት ለመውጣት ከቀሩት ሶስት ጨዋታዎች በሜዳው በሚያከነውናቸው ሁለቱ ጨዋታዎች ላይ እምነት ጥሏል። ከነዚህ ውስጥ ቀዳሚው ደግሞ ነገ አዳማ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይሆናል። ሊጉን ለሶስት ቀናት የመምራት ዕድል ገጥሞት የነበረው አዳማ ከተማ ምንም እንኳን ከዋንጫ ፉክክሩ ገሸሽ ቢልም አሁንም ተስፋው አልተሟጠጠም። ይህን ጨዋታ በድል መወጣት ከቻለ በቀሪዎቹ ሁለት ሳምንታት ከሊጉ መሪዎች ጋር እርስ በእርስ የሚገናኝ በመሆኑ የመጨረሻ ዕድሉን ለመሞከር አጋጣሚው ይፈጠርለታል። ይህ ሲታሰብ አዳማ ከተማ ከጨዋታው የሚያገኘው ነጥብ ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ የመውረድ ስጋት ላንዣበበባቸው በለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆን መናገር ይቻላል።

የረጅም ጊዜ ቅጣት ላይ ከሚገኙት ግብ ጠባቂው በረከት አማረ እና አሳሪ አልመሀዲ ውጪ ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ሙሉ ቡድናቸው ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆን በአዳማ በኩል ደግሞ ሱራፌል ዳኛቸው ጉዳት ላይ የሚገኝ ብቸኛው ተጨዋች ነው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– አዳማ ላይ በ13ኛው ሳምንት የተጋናኙበት የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸው ባለሜዳዎቹ ከሙሉ ብልጫ ጋር 3-0 በሆነ ውጤት ያሸነፉበት ነበር።

– ሽረ ላይ እንዲቀጥል የተደረገውን ጨዋታ ጨምሮ ወልዋሎ ዓ.ዩ ከመጨረሻ አራት የሜዳው ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በሁሉም ጨዋታዎች ግብ ቀንቶታል።

– አዳማ ከተማ ከሜዳው በወጣባቸው የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች ሶስቴ ሽንፈት ገጥሞት አንድ ጊዜ አቻ ቢለያይም የሲዳማው ሽንፈቱ በፎርፌ ተካክሶለታል።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት እንደሚመራው ታውቋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

የመጨረሻ የሊግ ጨዋታዎቻቸውን በሽንፈት ያገባደዱት ሁለቱ ክለቦች አሁን ደግሞ እርስ በእርስ ይገናኛሉ። አዲስ አበባ ላይ በ25ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ በደደቢት 2-1 የተሸነፈው አርባምንጭ ያስያዘው የተጨዋች ተገቢነት ክስ ካልተሳካ በቀር አሁን ያለበት 15ኛ ደረጃ እጅገን የሚያሰጋው ነው። ምንም እንኳን ወላይታ ድቻን ያስተናገደበት ጨዋታ ያለግብ ቢጠናቀቅም ቡድኑ ሜዳው ላይ ያሳይ የነበረው ጥንካሬ ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥቦችን ስለማግኘት እንዲያስብ የሚያደርገው ነው። ከሜዳው ሲወጣ እጅግ ለሚቸገረው ሀዋሳ ከተማ ደግሞ የተጋጣሚው የሜዳ ጥንካሬ ስጋት ላይ የሚጥል ነው። በአካባቢው በነበረው የፀጥታ ሁኔታ ልምምድ እስከማቋረጥ ደርሶ የነበረው ሀዋሳ ከተማ በኢትዮጵያ ቡና የደረሰበት የ 5-1 ሽንፈት ደግሞ ለተዳከመው የቡድኑን ወቅታዊ አቋም ተጨማሪ መጥፎ ትዝታን አሳርፎበታል። ባለፉት አራት ሳምንታት በአንድ ብቻ የጨመረው የነጥብ ስብስቡም ሳይታሰብ ወደ አደጋው ክልል አቅርቦታል። በመሆኑም አርባምንጭ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ሀዋሳ ከተማም ተጋጣሚው ከደረሰው ዕጣ ለመራቅ ጠንከር ያለ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

አርባምንጭ ከተማዎች ያለምንም የጉዳት እና ቅጣት ዜና ለጨዋታው የደረሱ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ ሶሆሆ ሜንሳህን በቅጣት አዲስአለም ተስፋዬን ደግሞ በጉዳት የማያሳልፍ ይሆናል። ከዚህ ውጪ በመኖሪያ ፍቃድ መጠናቀቅ ምክንያት ወደ ሀገሩ ያቀናው ሲላ መሀመድም የማይኖር ሲሆን ደስታ ዮሀንስ ደግሞ ከጉዳት የተመለሰ ነገር ግን ለጨዋታው መድረሱ አጠራጣሪ የሆነ ተጨዋች ነው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች 13 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ 5 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚው ነው። 5 ጊዜ አቻ ሲለያዩ በ3 ጨዋታዎች አርባምንጭ አሸናፊ ሆኗል። ሀዋሳ 16፣ አርባምንጭ 12 ጊዜ አሸንፈዋል።

– አርባምንጭ ላይ 6 ጊዜ ተገናኝተው አርባምንጭ 3 ፣ ሀዋሳ 1 ድል አስመዝግበዋል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

– አርባምንጭ ከተማ በሁለተኛው ዙር ሜዳው ላይ ግብ ያልተቆጠረበት ሲሆን በአምስቱ ጨዋታዎች 11 ግቦችን ከመረብ አገናኝቶ የጣለው ሁለት ነጥቦች ብቻ ነው።

– በገለልተኛ ሜዳ የተደረገውን የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ጨምሮ ሀዋሳ ከተማ ከሜዳው በወጣባቸው አራት የመጨረሻ ጨዋታዎች ያሳካው ከድሬደዋ ያገኘውን አንድ ነጥብ ብቻ ነው።

ዳኛ

– ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የመምራት ሀላፊነት ለኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ተሰጥቷል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ፋሲል ከተማ

የአዲስ አበባው ስታድየም የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ውጤት ጠቃሚነቱ ለባለሜዳዎቹ ያመዝናል። ከሀዋሳ እና ድሬዳዋ ያገኛቸው አራት ነጥቦች ተስፋ የሰጡት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ቢገኝም የዚህ ጨዋታ ውጤት ነገሮችን ሊቀይሩለት ይችላሉ። ላለፉት በርካታ አመታት በመጨረሻ ሳምንታት በሚደረጉ ጨዋታዎች ከመውረድ የሚተርፈው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዘንድሮም ልምዱን ተጠቅሞ በሊጉ ለመቆየት ሜዳው ላይ ከሚያደርጋቸው ሁለት ጨዋታዎች መካከል አንዱ ከሆነው ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት እጅግ አስፈላጊው ነው። በዚህ ረገድ ጥሩ ዜና የሚሆነው ተጋጣሚው ፋሲል ከተማ በሁለቱም ፉክክሮች ውስጥ የማይገኝ መሆኑ ነው። አፄዎቹ የያዙት 38 ነጥብ ከዋንጫ ፉክክሩ ሙሉ ለሙሉ ያስወጣቸው ቢሆንም ከወራጅ ቀጠናው ግን በእጅጉ ርቀዋል። ይህ እንዲሆን ያስቻለው ደግሞ ቡድኑ ከስድስት ሳምንታት በኋላ የማሸነፍ እና ግብ የማስቆጠር ረሀቡን ያስታገሰበት የሲዳማ ቡናው የ2-1 ድል ነው። ሆኖም ቀጣዮቹ ጨዋታዎች ቡድኑ የአምና ውጤቱን ለማሻሻል የሚያስብባቸው እና አሰልጣኙም የቀጣይ አመት ዕቅዳቸውን ካሁኑ ማጤን የሚጀምሩባቸው እንደሆኑ ይጠበቃል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና ሙሉ ስብስቡን ይዞ ፋሲል ከተማን ያስተናግዳል። ሆኖም እንግዶቹ ከጉዳት ዝርዝር የማይጠፉት የመሀል ተከላካዮቹ ዐይናለም ኃይለ እና ያሬድ ባየህን ሳይዙ ነው ወደ መዲናዋ ያቀኑት።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች 4 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ኤሌክትሪክ 1 ጊዜ አሸንፎ በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ሁለቱም ሶስት ጎሎች አስቆጥረዋል።

– አዲስ አበባ ላይ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል አንዱን ሲያሸንፍ ኤሌክትሪክ ሌላኛውን አሸንፏል።

– ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሁለተኛው ዙር አራት የክልል ቡድኖችን ያስተናገደ ሲሆን ሶስቱን አሸንፎ ከአንዱ ነጥብ ተጋርቷል።

– ፋሲል ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ በአዲስ አበባ ስድታየም ካደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች ማሳካት ችሏል።

ዳኛ

– ጨዋታው በፌደራል ዳኛ ጌቱ ተፈራ መሪነት ይከናወናል።