ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወራጅ ቀጠናው የወጣበትን ድል አግኝቷል

በአዲስ አበባ ስታድየም በቀዳሚነት የተደረገው የሊጉ የ28ኛ ሳምንት መርሀ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ፋሲል ከተማን አገናኝቶ በባለሜዳዎቹ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቡድኖቹ በ27ኛው ሳምንት ካደረጓቸው ጨዋታዎች አንፃር በመጀመሪያ አሰላለፋቸው ውስጥ ለውጦችን አድርገዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከድሬዳዋ ከተማ ነጥብ ተጋርቶ ከተመለሰው ቡድናቸው ውስጥ ዘካርያስ ቱጂ እና ታፈሰ ተስፋዬ አስቀምጠው ዐወት ገ/ሚካኤል እና ዲዲዬ ለብሪን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሲያካትቱ ተጋጣሚያቸው ፋሲል ከተማ ደግሞ ሲዳማ ቡናን ከረታበት ጨዋታ የአራት ተጨዋቾች ለውጥ አድርጓል። በዚህም መሰረት አማካይ መስመር ላይ ሙሉቀን አቡሀይ እና ኤፍሬም አለሙ በይስሀቅ መኩሪያ እና ያስር ሙገርዋ ሲተኩ ፊት መስመር ላይ ደግሞ ሀሚስ ኪዛ እና ኤርሚያስ ኃይሉ በመሀመድ ናስር እና ፍሊፕ ዳውዝ ምትክ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ጨዋታው ከወጣለት መርሀ ግብር በ14 ደቂቃዎች ዘግይቶ የጀመረ ነበር። አስቀድሞ የጣለው በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ለመዘግየቱ ምክንያት የነበረ ሲሆን ሜዳው ላይ ከተኛው ውሀ አንፃር ጨዋታው ላይካሄድ ይችል የነበረበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር። የሜዳው ሁኔታ ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ እርጥበቱ እስኪቀንስ በነበሩት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ኳስን በመያዝ እና የተጨዋቾችን ግምት በማዛባት ቡድኖቹ ስህተት ለመስራት የተረርቡባቸውን ሁነቶች አስመልክቶናል። ኤርሚያስ ኃይሉ እና ራምኬል ሎክ ከፋሲል ከተማ ዲዲዬ ለብሪ እና ኃይሌ እሸቱ ወደ ግብ የቀረቡባቸው እንቅስቃሴዎችም ወደ ሙከራነት ሳይቀየሩ በመሀል የቀሩ ነበሩ።

ምንም እንኳን የሜዳው ሁኔታ ጉልበት የሚፈልግ እና ቡድኖቹ ባሰቡበት መንገድ እንዲጫወቱ የሚፈቅድ ባይሆንም የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ፉክክርን አስመልክቶናል። የተከላካይ ክፍላቸውን ወደ መሀል ሜዳ የማስጠጋት ድፍረት የነበራቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ መስመር በመላክ እና ወደ ውስጥ በማሻማት ላይ ያመዘኑ ሲሆን በተለይ ኃይሌ እሸቱ ከግራ መስመር ለማሻማት የሞከራቸው ኳሶች ለቡድኑ የመጀመሪያ ሙከራ ለማስገኘት የሚያበቁ ነበሩ። ወደ ራሳቸው ግብ ቀርበው መከላከልን የመረጡት ፋሲሎች ደግሞ በብዛት በኢትዮ ኤሌክትሪክ ሜዳ ላይ ለሚቀሩት አጥቂዎቻቸው በረጅሙ የሚልኳቸው ኳሶች ጥሩ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩላቸውም አጥቂዎቹ እስከ ግብ ገፍተው ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት በሜዳው ሁኔታ እክል ገጥሞታል። 8ኛው ደቂቃ ላይ ካሉሻ አልሀሰን ከአዲስ ነጋሽ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ ተከላካዮች የተደረቡበት እንዲሁም 10ኛው ደቂቃ ላይ ሀሚስ ኪዛ በኤሌክትሪክ ሳጥን መግቢያ ላይ ተከላካዮችን አሸማቆ ለመምታት ሲሞክር በግርማ በቀለ ጥፋት የተሰራበት አጋጣሚዎች ቡድኖቹን ወደ መሪነት ያቀረቡ ቅፅበቶች ነበሩ።

ኤሌክትሪኮች በተጋጥሚያቸው አጋማሽ በመቆየት ጫና በፈጠሩባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች ያለቀለት የግብ ሙከራ ያልፈጠሩ ሲሆን ፋሲሎች ሀሚስ ኪዛ 18ኛው ደቂቃ ላይ ካደረገው የርቀት ሙከራ የተሻለ ወደ ግብ ክልል ደርሰዋል። ከፍ ያለ ፍትጊያ እየታየበት በቀጠለው ጨዋታ 27ኛው ደቂቃ ላይ ፌደራል ዳኛ ጌቱ ተፈራ ወደ ፋሲል ከተማ የተላከውን ኳስ ፍፁም ከበደ ለግብ ጠባቂው በደረቱ ለማቀበል በሞክረበት ወቅት በእጁ ነክቷል በማለት ለኢትዮ ኤሌክትሪክ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል። ከፍተኛ ተቃዎሞ የገጠመው የአርቢትሩ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔ በአዲስ ነጋሽ አማካይነት ወደ ግብ ሲቀየር አምሳሉ ጥላሁን ከተጠባባቂ ተጨዋቾች መሀል በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣም ጭምር መንስኤ ሆኖ አልፏል። 

ፋሲል ከተማዎችም ቅሬታቸውን ክስ በማስያዝ ጭምር ገልፀዋል። ኤሌክትሪኮች ይህችን ግብ ካገኙ ሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሚካል ሳማኬ በሚገባ ካላረቀው ኳስ ካሉሻ አልሀሰን ራሱን ግብ ጠባቂውን እና ተጨማሪ ተከላካይ ካታለለ በኋላ ወደ ግብ የላከው ኳስ በግቡ ቋሚ ተመልሷል።
ከመመራታቸው አስቀድሞ ያደርጉ እንደነበረው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የተከላካይ መስመር ጀርባ ወደ መስመሮች ያደሉ ኳሶችን መጣላቸውን የቀጠሉት ፋሲሎች 39ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ራምኬል በተመሳሳይ መልኩ ያገኘውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻማ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደረገው ሀሚስ ኪዛ በሁለት ተከላካዮች መሀል ሆኖ ወደ ግብነት ቀይሮታል። 

ሆኖም ፋሲልምች አቻ መሆን የቻሉት ለቀጣዮቹ አምስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር። ኤሌክትሪኮችም በረጅሙ ወደ ፋሲል የግብ ክልል የላኩት ኳስ የበሀይሉ ተሻገር እና ዲዲዬ ለብሪ ድንቅ መናበብ ተጨምሮበት በመጨረሻም በዲዲዬ ለብሪ አማካይነት ወደ ግብነት ተለውጧል። ይህ ጎል ከመቆጠሩ በፊት ራምኬል ሎክ የመጨረሻ የግብ ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረ ሲሆን ባለሜዳዎቹ 2-1 እየመሩ የመጀመሪያው አጋማሽ እንዲያልቅ ሆኗል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ዝቅተኛ ፉክክር ያስተናገደው ሁለተኛው የጨዋታ ጊዜ ለኢትዮ ኤሌክትሪኮች ተጨማሪ ግቦችን አስገኝቷል። በተለይም በዚህ አጋማሽ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የታየው ዲዲዬ ለብሪ ደግሞ የባለሜዳዎቹ ዋንኛ የማጥቃት አማራጭ ነበር። ተጨዋቹ በረጅሙ የሚላኩለትን ኳሶች ከግራ መስመር በመነሳት ወደ ውስጥ ይዞ በመግባት እንዲሁም በቀጥታ በማሻማት ለፋሲሉ የቀኝ መስመር ተከላካይ ሰይድ ሁሴን ፈተና መሆን ችሏል። በተመሳሳይ እንቅስቃሴ 54ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ ተነስቶ በፋሲል ሳጥን ውስጥ ተገኝቶ ተጨዋቾች ለማለፍ ሲሞክር ጥፋት ተሰርቶበት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሌላ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝቷል። እንደመጀመሪያው ሁሉ አሁንም የቡድኑ አምበል አዲስ ነጋሽ ኳሷን አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ከፍ አድርጓል።

ፋሲል ከተማዎች በሁለት ግቦች ልዩነት ቢሩም የሚሰነዝሯቸው ድንገተኛ ጥቃቶች ውጤት ለመቀየር ሲቃረቡ ይታይ ነበር። 60ኛው ደቂቃ ላይ ያስር ሙገርዋ ከቀኝ መስመር ቅጣት ምት ያደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ እና ሀሚስ ኪዛ ከሲሴ ሀሰን ጀርባ የተጣለን ኳስ ይዞ በመግባት ከሱሊማና አቡ ጋር ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነበሩ። ሆኖም 61ኛው ደቂቃ ላይ ኤሌክትሪኮች ወደ ግራ መስመር የጣሉት ረጅም ኳስ በዲዲዬ ለብሪ አማካይነት ወደ ኋላ ሲመለስ ካሉሻ አልሀሰን አራተኛ ግብ አድርጎት የቡድኑን መሪነት ማስፋት ችሏል። 

ተቀዛቅዞ በቀጠለው ጨዋታ 70ኛው ደቂቃ ላይ በካታንጋ በኩል የነበሩ የፋሲል ከተማ ደጋፊዎች መስመር ዳኛው ላይ ቁሳ ቁሶችን በመወርወራቸው ለአራት ደቂቃዎች የተቋረጠው ጨዋታ ከድር ኃይረዲን እና ይስሀቅ መኩሪያ ደጋፊዎችን ካረጋጉ በኋላ እንዲቀጥል ሆኗል። በቀሪ ደቂቃዎች አብዱርሀማን ሙባረክ እና ናትናኤል ጋንቹላን ቀይረው በማስገባት ሁለቱ መስመሮች ላይ ትኩረት አድርገው ለማጥቃት የሞከሩት ፋሲል ከተማዎች ተፅዕኗቸው የወረደ ሲሆን ከወገብ በላይ ያሉ ተሰላፊዎቻቸውን በተጋጣሚ ሳጥን አቅራቢያ አድርገው ረጃጅም ኳሶችን ይጥሉ የነበሩት ኤሌክትሪኮችም ጫናቸው ቀንሶ ጨዋታው የውጤት ለውጥ ሳያሳይ በባለሜዳዎች የ4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በአመቱ ለሁለተኛ ጊዜ በአንድ ጨዋታ አራት ግቦች ያስቆጠረው ኢትዬ ኤሌክትሪክ ነጥቡን 32 አድርሶ የነበረበትን 14ኛ ደረጃ ለድሬዳዋ ከተማ አስረክቦ ወደ 12ኝነት ከፍ ሲል ፋሲል ከተማ በ6ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ም/አሰልጣኝ ቦጋለ ዘውዴ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ጨዋታው ለኛ በጣም አስፈላጊያችን ነበር። ወራጅ ቀጠና ውስጥ የለን በመሆኑ የግድ ማሸነፍ ነበረብን። በዚህ አስቸጋሪ ሜዳ ላይ ተጨዋቾቻችን ለማሸነፍ ላሳዩት ከፍተኛ ተጋድሎ ምስጋና ይገባቸዋል። በአጠቃላይ ጥሩ ነበርን ማለት እችላለሁ። በቀጣይም ሌሎቹን ቡድኖች ሳንጠብቅ የራሳችንን ጨዋታዎች እናሸንፋለን።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – ፋሲል ከተማ

ከኛ በተሻለ እነሱ ጫና ለማሳደር ሲሞክሩ ነበር። እኛም ጎሎች አግብተናል። ሆኖም ወደ መጨረሻ ላይ ግቦችን አስቆጥረውብናል። ከዛ በኋላም ግቦችን ለማስቆጠር ሞክረን ነበር። በጥቅሉ ግን ጨዋታው ምንም አይልም። ቡድናችን በተለይም ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች መሻሻልን እያሳየ እንደሆነ ይሰማኛል።