ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊጉን መምራት ጀምሯል

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 28ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች መካከል የመጨረሻ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ በባለሜዳዎቹ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

11:30 በመረው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዋንጫ ፉክክሩ ላለመውጣት ወላይታ ዲቻ ደግሞ ከሊጉ ላለመውረድ የሚያደርጉት ፍልሚያ እንደመሆኑ ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም ግምቶችን ሁሉ ፉርሽ አድርጎ የአንድ ቡድን የበላይነት ብቻ ታይቶበት አልፏል። ጨዋታው እንደተጀመረ ሁለቱም  ቡድኖች ኳስን ተቆጠቀጥሮ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ የፈለጉ በሚመስል መልኩ ሙራዎችን ያደረጉ ሲሆን በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የሚያገኟቸውን ኳሶች ወደ መስመር በማውጣት ጫናዎችን በመስመር በኩል ለመፍጠር ሲጥሩ ታይቷል። በ4ኛው ደቂቃ ጃኮ አራፋት ከርቀት ሞክሮት ወደ ውጪ የወጣበት አጋጣሚ የጨዋታው የመጀመሪያ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሲሆን ኳሷ ኢላማዋን ስታ ወደ ውጪ ወጥታለች። ከአራት ደቂቃዎች በኃላ ባለሜዳዎቹ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው በበኃይሉ አሰፋ አማካኝነት የግብ ማግባት እድል አግኝተው የነበረ ሲሆን በኃይሉ ኳሷን እየገፋ ወደ ተጋጣሚ  ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በመግባት ለቡድን አጋሮቹ አቀብላለው ብሎ ወጣበት እንጂ ጥሩ አጋጣሚ አግኝተው ነበር።

በጨዋታው ጎሎችን ለማስቆጠር እጅግ ፈልገው ሲንቀሳቀሱ የታዩት ጊዮርጊሶች በተለያዩ ሁኔታዎች ጫናዎችን ማሳደራቸውን ቀጥለው በ24ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ግብ አግኝተዋል። ኃይማኖትወርቁ አሜ መሃመድ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት በኃይሉ አሰፋ አሻምቶት ሰልሃዲን በርጌቾ በግንባሩ ገጭቶ ጎል አስቆጥሮ መሪ መሆን ችለዋል። አሁንም በቀላሉ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ጊዮርጊሶች በ34ኛው ደቂቃ በኃይሉ አሰፋ ለአሜ መሃመድ የሰጠውን ኳስ አሜ ከበረኛ ጋር ተገናኝቶ ዕድሉን ያመከነ ሲሆን የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ልታደርግ የምትችል አጋጣሚ ነበረች። የመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ የበላይነት የወሰደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚውን ፍፁም ከጨዋታ ውጪ ማድረግ የቻለ ሲሆን ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥር ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ወላይታ ድቻዎች ተዳክመው የታዩ ሲሆን በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ተደራጅተው ሲጫወቱ አልተስተዋለም።

በሁለተኛው አጋማሽ በትንሹም ቢሆን ተጠናክረው የገቡት ድቻዎች በኃይማኖት ወርቁ አማካኝነት ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ከርቀት ሙከራ አድርገው የነበረ ሲሆን ኳሷ ኢላማዋን ስታ ወደ ውጪ ወታለች። በሜዳው አለመመቸት ምክንያት ብልጠት የተሞላበት የጨዋታ አቀራረብ ይዘው የገቡት ጊዮርጊሶች በ56ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል ያስቆጠሩ ሲሆን በኃይሉ አሰፋ የተጋጣሚው የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ብቻውን ኳስ አግኝቶ ተረጋግቶ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።

ከ60ኛው ደቂቃ በኃላ በስታዲየሙ ዝናብ በመጣሉ ሁለቱም ቡድኖች ተፈትነው ያመሹ ሲሆን በተለይ የወላይታ ዲቻ ተጨዋቾች ኳሷን ለመግፋት እንኳን ሲቸገሩ ታይቷል። በ70ኛው ደቂቃ ኦዝቫልዶ ታቫሬዝ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ በሚገባ ተቆጣጥሮት ሶስተኛ ግብ ለቡድኑ ያስቆጠረ ሲሆን የቡድኑንም በራስ መተማመን ከፍ ማድረግ ችሏል። አሁንም ጎል ያልጠገቡ የሚመስሉት ጊዮርጊሶች ግብ ለማስቆጠር ሙከራቸውን የቀጠሉ ሲሆን በ85ኛው ደቂቃ የቡድኑን የመጀመሪያ ግብ ያስቆጠረው ሳላዲን በርጌቾ ለራሱ ሁለተኛ የቡድኑ ደግሞ አራተኛ ግብ በግንባሩ ያስቆጠረ ሲሆን በስታዲየም የሚገኙት ደጋፊዎችንም በደስታ አስፈንድቋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ተጋባዦቹ ከባዶ ከመሸነፍ የሚያድናቸውን ጎል ለማስቆጠር የጣሩ ቢሆንም ሳይሳካላቸው እጅ ሰጥተው ከሜዳ ወጥተዋል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ጨዋታው እጅግ ጥሩ ነበር። እንደተለመደው ጨዋታውን በሚገባ ተቆጣጥረን የግብ እድሎችን ከተለያዩ አማራጮች ለመፍጠር ስንሞክር  ነበር። ይሄ ደግሞ የምንፈልገውን እንድናገኝ ረድቶናል።በጨዋታው ቀጥተኛ ለመሆን ሞክረናል ይህ ደግሞ ሜዳው እኛ የምንፈልገውን አጫጭር ቅብብሎች እንድናደርግ አያደርገንም። ስለዚህ ከጨዋታው ውጤት ለማግኘት ስንል አጨዋወታችንን ቀጥተኛ ለማድረግ ሞክረናል። ተጋጣሚያችን ውጤቱን እነደሚፈልገው እናውቅ ነበር። ያ ደግሞ ጠንክረን እንድንጫወት እና በትኩረት እንድንቀሳቀስ አድርጎናል። እንደ አሰልጣኝነቴ ዋንጫውን እንደምናነሳ አምናለሁ። ቀጣይ ያሉብንን ፈተናዎች  አልፈን ዋንጫውን እናነሳለን የሚል እምነት አለኝ።

አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ – ወላይታ ድቻ

ጨዋታው እጅግ ፈትኖን ነበር። የተጋጣሚያችን የተሻለ መሆን እና የሜዳው አለመመቸት ውጤት እንድናጣ አድርጎናል። ሜዳው እኛ ያሰብነውን አጨዋወት እንዳናደርግ አድርጎናል። ተጨዋቾቼ ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ሲሞክሩ ኳሶች ይበላሹባቸው ነበር። ይህ ደግሞ ተጨዋቾቼ ያላቸውን አቅም አውጥተው እንዳይጫወቱ አድርጎቸዋል። ቡድናችን አስጊ ደረጃ ላይ ነው ያለው ያንን እናውቃለን። ከዚህ በኃላ ያሉብንን ጨዋታዎች ለማሸነፍ እና በሊጉ ለመቆየት ያለንን ሁሉ እናደርጋለን።