አርባምንጭ በሜዳው ነጥብ ጥሎ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 28ኛ ሳምንት መርሐ ግብር አርባምንጭ ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ ጨዋታውን ያለ ጎል በአቻ ውጤት አጠናቆ በወራጅ ቀጠናው ላይ ለመቆየት ተገዷል።
አርባምንጭ ከተማ 4 3 3 አሰላለፍ ይዞ ሲገባ ለዚህ እንዲረዳውም ደደቢትን ከገጠመው ስብስብ ብርሃኑ አዳሙን በፍቃዱ መኮንን፣ አሌክስ አማዙን ደግሞ በአንድነት አዳነ ቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቷል። ሀዋሳ ከተማ በ4-5-1 አሰላለፍ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ከተጠቀማቸው ተጫዋቾች መሳይ ጳውሎስ፣ ጌትነት ቶማስ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና ያቡን ዊሊያምን በማሳረፍ ወንድማገኝ ማዕረግ፣ ዮሃንስ ሰጌቦ፣ አስጨናቂ ሉቃስ፣ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን እና አላዛር ፋሲካ በምትካቸው በማስገባት ወደ ሜዳ ገብቷል።

ፍጥነት የታከለበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከና ከጅምሩ ጥሩ እንቅስቃሴ ታይቶበታል። አለልኝ አዘነ ከርቀት ያደረገው የ4ኛ ደቂቃ ሙከራ የመጀመርያው የጎል አጋጣሚ ነበር። በ13ኛ ደቂቃ ላይ ፀጋዬ አበራ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት አለልኝ አዘነ ሞክሮ በግብ ጠባቂው ተይዞበታል። መከላከልን ምርጫቸው አድርገው ወደ ሜዳ የገቡት ሀዋሳ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት ታፈሰ ሰለሞን ይዞ የመጣውን ኳስ ለላውረንስ ሲያቀብል ጋናዊው ተከላካይ ወደግብነት ቀየረው ሲባል ጽዮን ለመያዝ ሞክሮ  ከእጁ ሲያመልጠው አጠገቡ የነበረው ወርቅይታደስ አበበ ወደ ውጪ ለማውጣት ሲዘጋጅ እስራኤል እሸቱ በፍጥነት መትቶ ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥታበታለች።

አርባምንጭ ከተማዎች በተደራጀ የመከላከል ሲስተም ሲጫወቱ የነበሩት የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮችን በር ለመድፈር የአየር ላይ ኳሶችን ለመጠቀም ተገደዋል። 20ኛው ደቂቃ እንዳለ ከበደ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ፀጋዬ አክርሮ መትቶ ወደ ውጪ ሲወጣበት በድጋሚ እንዳለ ከበደ አመቻችቶ ለፍቃዱ መኮንን አቀብሎት ወደ ጎል ሲመታ ኳስ ተጨርፎበት አለልኝ አዘነ በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ፀጋዬ አበራ አቀብሎ ፀጋዬ ወደ ውጪ አውጥቶታል። አርባምንጮች በ28ኛው ደቂቃ አማኑኤል በሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች ተደርባ የመጣችውን ኳስ አገባ ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ውጪ የመታውና 43ኛ ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል ለፍቃዱ የደረሰው ኳስ ፍቃዱ አገባ ተብሎ ሲጠበቅ ዩሀንስ ሰጌቦ ከመስመር ያወጣት ኳስ በጣም የሚያስቆጩ ነበሩ።

ሀዋሳ ከተማዎች በመጀመርያው አጋማሽ የፈጠሩት የግብ እድል ጥቂት ሲሆን እስራኤል የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ በረጅሙ ጎል ሞክሮ በጽዮን መርዕድ የተያዘበት የሚጠቀስ ነው። በጭማሪ ደቂቃ ላይ አርባምንጭ ከተማዎች በወርቅይታደስ ረጅም ኳስ የፈጠሩትን እድል ፍቃዱ መኮንን መጠቀም ሳይችል ቀርቶ የመጀመርያው አጋማሽ ያለግብ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመርያው አጋማሽ እንቅስቃሴ የተሻለ የነበረ። ሀዋሳ ከተማዎችም በመጠኑ ለማጥቃት የሞከሩ ሲሆን አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ ጥሩ እድል ያባከኑበት ሆኖ አልፏል። በዚህ ረገድ በ48ኛው ደቂቃ እንዳለ ከበደ ከረጅም ርቀት ሞክሮ የሳተው እና አማኑኤል ጎበና ከማዕዘን የተሻገረለትን ኳስ አክርሮ መቶ በሀዋሳ ተከላካዮች በግንባር የተመለሰበት ሙከራ ተጠቃሽ ናቸው።በዚህ ሁሉ አጋጣሚ ግን ሀዋሳ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት እየሄዱ በሚፈጥሩት ቸልተኝነት የአርባምንጭ ተከላካዮች ሲነጥቋቸው ይታይ ነበር። በተለይ ፍሬው ሰለሞን የሚያገኛቸው ዕድሎች ለቡድኑ በጣም የሚያስቆጩ ነበሩ።

የጨዋታውን ውጤት መቀየር የምትችለውን እና አወዛጋቢ የነበረችው ፍጹም ቅጣት ምት ለአርባምንጭ ከተማዎች የተሰጠችውም በዚሁ ሁለተኛ አጋማሽ 67ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። አርቢትሩ ፍፁም ቅጣት ምቷን የሰጡት የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ፀጋዬ አበራን ጎትቶታል በማለት ነበር። ሆኖም እንዳለ ከበደ መቶ ተክለማርያም ሻንቆ መልሶበታል። ከዚህ በኋላም አርባምንጭ ከተማዎች በተደጋጋሚ የሀዋሳ የግብ ክልል ውስጥ በመመላለስ የግብ እድል ለመፍጠር ሲጥሩ ቆይተዋል። በ82ኛው እና በ89ኛው ደቂቃዎች ላይ ብርሃኑ አዳሙ በአንድ ሁለት ቅብብል የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ቀየረ ተብሎ ሲጠበቅ ግብ ጠባቂው የመለሰበት ፣ ተመስገን ካስትሮ ከተካልኝ የተሻገረልትን ኳስ ወደ ጎል መቶ በግቡ ቋሚ የወጣበት እጅግ የሚያስቆጩ ሙከራዎች ነበሩ። የጨዋታው መጠናቀቅያ ላይ ሀዋሳ ከተማዎች ያለቀለት ኳስ አግኝተው ያቡን አገባ ሲባል ወርቅይታደል ተንሸራቶ አውጥቶበታል። በዚህ መልኩ ጨዋታው ያለግብ ሲጠናቀቅ አርባምንጭ ከተማዎች በሊጉ ለመቆየት የቀሩትን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ እና የሌሎች ክለቦችን ውጤት መጠበቅ ግድ ሆኖበታል። ተጋጣሚው ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ወሳኝ ነጥብ አስመዝግቦ ተመልሷል። የጨዋታው ማብቂያ ላይ የአርባምንጭ ከተማ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ሲያለቅሱ ተመልክትናል።


የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ

ጨዋታው እንደተመለከታቹት ነበር። አንድ ነጥብ ፈልገን ነበር የገባነው ተሳክቶልናል። ነገር ግን ያገኘናቸው አጋጣሚዎችም የሚያስቆጩ ነበሩ።

* የአርባምንጭ አሰልጣኞች አስተያየት አልሰጡም።