ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ

በ28ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ነገ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን የሚስተናግድበትን ጨዋታ እንደሚከትለው ዳሰነዋል።

ዛሬ የተደረጉት የሊጉ መርሀ ግብር ውጤቶች የነገዎቹን ሁለቱ ተጋጣሚዎች ጫና ውስጥ የሚከቱ ናቸው። ኢትዮጵያ ቡና የተከታዮቹ መቐለ ከተማ እና አዳማ ከተማ ሽንፈት ባለበት ቆይቶ ለዚህ ጨዋታ እንዲደርስ ቢያግዘውም ከበላዩ ያሉት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባ ጅፋር ድል ግን አሁንም ጫና የሚያሳድርበት ነው። ሁለቱ ቡድኖች ያስቆጠሯቸው ግቦች መበራከት ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናም ተመሳሳይ ውጤት እንዲያስመዘግብ የሚያስገድደው ነው። ድሬዳዋ ከተማም ቢሆን የአርባምንጭ ከተማ ነጥብ መጣል ጥሩ ዜና ቢሆንለትም የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ አሸናፊነት ደግሞ ላለመውረድ የሚያደርገውን ትግል አክብዶበታል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያገኙት ብርቱካናማዎቹ ዛሬ ተመልሰው ከገቡበት የወራጅ ቀጠና ለመውጣት ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ግድ ይላቸዋል። ሶስት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቦ ለዚህ ሳምንት የደረሰው ኢትዮጵያ ቡናም ይህን ጨዋታ በድል በመወጣት እና መሪዎቹን በሁለት ነጥብ ርቀት መቅረብ ለድርድር የሚቀርበው ሀሳብ አይደለም። እነዚህ ቡድኖቹን ግዴታ ውስጥ የከተቱ ሁኔታዎችም ጨዋታው ከፍተኛ ፍልሚያ የሚደረግበት ሊሆን እንደሚችል የሚያመላክቱ ናቸው።

ኢትዮጵያ ቡና ከአቡበከር ነስሩ ባሻገር ቶማስ ስምረቱን በጉዳት የሚያጣ ሲሆን ምንም የጉዳት ዜና ያልተሰማበት ድሬዳዋ ከተማ በኩል ዮሴፍ ድንገቶ እና በረከት ይስሀቅ ከጉዳት ይመለሳሉ።

ዛሬ የአዲስ አበባ ስታድየም ያስተናገዳቸው ሁለት ጨዋታዎች ሁሉ ይህም ጨዋታ በርካታ ግቦችን የሚያስተናገድበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። በተለይም የተጨዋቾችን ግምት የሚያዛባው እና የኃላ መስመር ተጨዋቾችን ለስህተት የሚዳርገው የወቅቱ እጅግ የተበላሸ የመጫወቻ ሜዳ ለግቦች መንስኤ ሊሆን የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው። በአጨዋወት ደረጃ ደግሞ የሜዳው ምቹ አለመሆን ከሚፈጥራቸው የቅብብል ስህተቶች አንፃር ኳስን መስርቶ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የሚታሰብ አይመስልም። በዚህ ረገድ የተሻለ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በፈጣን ሽግግር የመስመር አጥቂዎቻቸውን ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴን ስለመተግበር እንደሚያስቡ ይገመታል። ከመስመር ተከላካዮቻቸው በቂ እገዛን የሚያገኙት ሚኪያስ መኮንን እና ሳሙኤል ሳኑሚ ወደ መሀል እየጠበበ የሚመጣ ጥቃት የግብ ዕድሎችን የመፍጠር አቅም እንደሚኖረው ይታመናል። በድሬዳዋ ከተማዎች በኩል የተጋጣሚያቸውን የመስመር እንቅስቃሴ ከመግታት ባለፈ ቀጥተኛ ኳሶችን ወደ ፊት ማድረስ የተሻለው አማራጫቸው ይመስላል። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ የፊት አጥቂዎቹ ኩዋሜ አትራም እና ሀብታሙ ወልዴ ጥሩ ጥምረትን በመፍጠር ከኢትዮጵያ ቡና የመሀል ተከላካዮች ጀርባ ለመግባት ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ባለፈ ከማዕዘን ምት እንዲሁም ከቅጣት ምት የሚነሱ ኳሶችም በክፍት ጨዋታ ከሚገኙ አጋጣሚዎች በተሻለ መልኩ ለሁለቱም ቡድንምች ግብ የማግኛ አማራጮች ሊሆኑ ይችላሉ።

የእርስ በእርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– በሊጉ የ13 ጊዜ ግንኙነታቸው 7 ጊዜ ኢትዮጵያ ቡና ሲያሸንፍ 4 ጊዜ አቻ ተለያይተው ድሬዳዋ ከተማ 2 ጊዜ አሸንፈዋል። ቡና 23፣ ድሬ 12 ጎል አስቆጥረዋል።

– አዲስ አበባ ላይ ላይ 6 ጊዜ ተገናኝተው ቡና አራቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተው ድሬዳዋ አሸንፎ አያውቅም።

– ኢትዮጵያ ቡና ከፍተኛ መሻሻል ባሳየባቸው የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ብቻ የጣለ ሲሆን ሶስቴ መረቡ ተደፍሮ አስር ግቦችን አስቆጥሯል።

– ድሬዳዋ ከተማ ካለፉት አምስት ጨዋታዎቹ ውስጥ ማሸነፍ የቻለው ሁለቱን ሲሆን ግብም ያስቆጠረው በነዚሁ ጨዋታዎች ነው።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃ/ስላሴ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።