ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ከድሬዳዋ ነጥብ ተጋርቶ የዋንጫ ተስፋውን አመንምኗል

በ28ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ እልህ አስጨረሽ ትግል ተደርጎበት ያለግብ ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ ቡና በተሰተካካይ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን 5-1 ከረታው ቡድኑ ውስጥ ጉዳት የገጠመው የመሀል ተከላካዩ ቶማስ ስምረቱ ምትክ ወንድይፍራው ጌታሁንን የተጠቀመ ሲሆን በተመሳሳይ የአንድ ተጨዋች ለውጥ ያደረገው ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለግብ ከተለያየበት ጨዋታ ጋናዊውን አጥቂ አትራም ኩዋሜን አስቀምጦ ለዳኛቸው በቀለ የመጀመሪያ አሰላለፍ እድል ሰጥቷል።

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ በተለምዶው ዳፍ ትራክ ተብሎ በሚጠራው መቀመጫ አካባቢ የደጋፊዎች ግጭት በመነሳቱ የፀጥታ ኃይሎች የስታድየሙን በሮች ዘግተው ተጨማሪ ደጋፊዎች እንዳይገቡ አድርገዋል። በመሆኑም በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎች የታጀበ እንዳይሆን ተገዷል። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የጣለው ከባድ ዝናብ ደግሞ ከዚህ በፊት ከነበረው እጅግ በባሰ ሁኔታ ሜዳውን ከማጨቅየት አልፎ ውሀ እንዲተኛበት ያደረገ ሲሆን ጨዋታው 11 ሰዐት ላይ የተከናወነ በመሆኑም በመጠኑ መጠጥ ብሎ ቢያንስ ትናንት የነበረበት ደረጃ ላይ እንዳይገኝ አድርጎታል።

ሳሙኤል ሳኑሚ በቀኝ መስመር ይዞ ገብቶ ወደ ውስጥ ከጣለው ኳስ ሚኪያስ መኮንን ከሳምሶን አሰፋ ጋር በተገናኛበት እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታው በሜዳው ሁኔታ ምክንያት በዛው ፍጥነት መቀጠል አልቻለም። 3ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ ቀኝ መስመር ዳኛቸው በቀለ ኳስ ይዞ ገብቶ ወደ ውስጥ ካሻማ እና ሀሪሰን ከያዘነት በኋላ ድሬዳዋ ከተማዎች ከተጋጣሚያቸው ተሽለው ታይተዋል። ወደ ጎን አስፍተው በሚቆሙት የፊት አጥቂዎቻቸው ሀብታሙ ወልዴ እና ዳኛቸው በቀለ እንቅስቃሴ በቡና የመስመር እና የመሀል ተከላካዮች መሀል ለመግባት ያሰቡ የሚመስሉት ድሬዎች ምንም እንኳን እስከ 15ኛው ደቂቃ በቡና አጋማሽ ላይ አመዝነው መንቀሳቀስ ቢቹሉም የመጨረሻ የሚባል የግብ ዕድል መፍጠር ግን አልተቻላቸውም። ባለፉት ጨዋታዎች ላይ በሁለቱ መስመሮች በሚያደርጉት ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ተጋጣሚን ያስጨንቁ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የገቡ ቢሆንም የሜዳው ሁኔታ ነገሮችን አክብዶባቸዋል። በ18 እና 19ኛው ደቂቃ በሳሙኤል ሳኑሚ እና ሚኪያስ መኮንን አማካይነት በተደረጉ ሙከራዎች ይበልጥ የተነቃቁት ቡናዎች በቀጣዮቹ ደዊቃዎች በተለይም ሚኪያስ መኮንን በተሰለፈበት የቀኝ መስመር አመዝነው ድሬዎችን ማስጨነቅ ችለዋል።

በነዚህ ኢትዮጵያ ቡና ተሽሎ በታየባቸው ደቂቃዎች ግን በብዛት ከርቀት ሙከራዎችን ያደርግ የነበረው ሳሙኤል ሳኑሚ በአራት አጋጣሚዎች ወደ ግብ ከላካቸው ኳሶች አንዱ ብቻ ነበር ኢላማውን የጠበቀው። 19ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሳምሶን ጥላሁን ከርቀት ያደረገውን ሙከራ ሳምሶን አሰፋ በአግባቡ ሳያድነው ቀርቶ ሚኪያስ መኮንን ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። ድሬዳዋ ከተማዎች የተወሰደባቸውን ብልጫ ተቋቁመው ወደ ፊት መሄድ የከበዳቸው ሲሆን ከ29ኛው ደቂቃ የዘነበ ከበደ ቅጣት ምት ውጪም ሌላ ሙከራ አላደረጉም። ለሁለቱም ቡድኖች እጅግ አስቸጋሪ የሆነው እና የኳሷን እንቅስቃሴ ከተጨዋቾች ግምት ውጪ እያደረገ ለተደጋጋሚ ግጭቶች ሲያጋልጣቸው የታየው የአዲስ ስታድየም ሜዳ ዕቅዶቻቸው ላይ ለውጦችን እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።

32ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡና በግራ መስመር ተከላካይነት ያሰለፈው አስናቀ ሞገስን በማስወጣት ባፒትስቴ ፋዬን አስገብቷል። በዚህም መሰረት እያሱ ታምሩ ለግራ መስመር አጥቂነት ወደኋላ የተመለሰ ሲሆን ፋዬ ሳሙኤል ሳኑሚ እና ሚኪያስ መኮንን ፊት መስመር ላይ ተቀላቅሏል። ከቅያሪው አንፃር ለፋዬ የሚላኩ ረጃጅም ኳሶች በብዛት እንደሚታዩ ቢጠበቅም 43ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ከግራ መስመር ከላከለት እና ቁመተ መለሎው አጥቂ ሳይደርስበት ከቀረው ኳስ ውጪ ሌላ ዕድል ሲፈጠር አልታየም። እንግዶቹ ድሬዳዋዎችም 38ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ድንገቶን በዳኛቸው ወርቁ በመቀየር የዕቅድ ለውጥ አድርገዋል። በዚህም መሰረት ድሬዎች ከፊት በሀብታሙ ወልዴን ብቻ በፊት አጥቂነት በማስቀመጥ አማካይ ክፍል ላይ ዮሴፍ ከኢማኑኤል ላሪያ ጎን በመሆን የተጋጣሚውን ወደ መስመር የሚወጡ ኳሶች እንዲያቋርጥ ሀላፊነት ሰጥተውታል። በዚህ ረገድ ቅያሪው ጥሩ ውጤት ቢያሳይም የቡድኑ የፊት መስመር ግን ተፅዕኖው ወርዶ የግብ ዕድል ሳይፈጥር የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

የጨዋታውን ክብደት በእጅጉ ከፍ ያደረገው አስከፊው የሜዳ ሁኔታ ቡድኖቹ ከጨዋታ ዕቅዳቸው በተጨማሪ ትጥቅም እንዲቀይሩ ያስገደዳቸው ነበር። ተጨዋቾች ከእረፍት ሲመለሱም በጭቃ የላቆጠ ዋና መለያቸውን በሁለተኛ መለያቸው በመቀየር ነበር። የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ድሬዳዋዎች ወደ ግብ ለመቅረብ ሀሳብ ያላቸው ያስመሰለ ቢሆንም በዛው የቀጠለ ግን አልነበረም። የኢትዮጵያ ቡና ማጥቃት መበርታት በጀመረባቸው ተከታይ ደቂቃዎች ድሬዎች ቀስ በቀስ ወደ ራሳቸው ግብ ለማፈግፈግ ተገደዋል። ሆኖም ኢትዮጵያ ቡናዎች በርካታ የማዕዘን ምቶችን ያገኙ ሲሆን ከየአቅጣጫው የሚላኩ ቀጥተኛ ኳሶችም ተጨማሪ የጥቃት አማራጮቻቸው ሆነዋል። የቡድኑ ተደጋጋሚ የአየር ላይጥቃት በድሬ ተከላካዮች እየራቀ ቆይቶ 57ኛው ደቂቃ ላይ ግን ቡናዎች ከባድ ሙከራ አድርገዋል። በዚህ አጋጣሚም ሳሙኤል ሳኑሚ ከቀኝ መስመር የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ አክርሮ ሲመታ ሳምሶን አሰፋ እና የግቡ ቋሚ ተጋግዘው አድነውበታል።

ጥቃቱ በበረታባቸው ቁጥር በራሳቸው ሳጥን ውስጥ የሚያሳለፉት ደቂቃ እየተበራከተ የመጣው ድሬዳዋዎች ተጋጣሚያቸውን ለተወሰኑ ደቂቃዎች ከግብ ክልላቸው እንዲርቅ ማድረግ ችለው የነበረ ቢሆንም ለማጥቃት ግን ቦታ አልነበራቸው። ከዚህ ይልቅ አንዱን ነጥብ ለማግኘት ሙሉ ለሙሉ በመከላከል ላይ ከመጠመድ ባለፈ ሰትዐ በማባከን እና ጨዋታውን በማዘግየትም ጭምር የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ ለማቆራረጥ ሞክረዋል። ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴም ተጨዋቼችን ከመገሰፅ ባለፈ ሶስት የቢጫ ካርዶችን አሳይተዋል። ቡድኑ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ከማዕዘን ምት በተነሳ እና ከሀሪሰን ሄሱ እጅ ካመለጠ ኳስ የግብ አጋጣሚ የፈጠረ ቢሆንም ከዚህ ውጪ በቡና የሜዳ ክልል ለመድረስ አልቻለም። 70ኛው ደቂቃ ላይ በአማኑኤል ዮሀንስ የረጅም ርቀት ቮሊ እና በ75ኛው ደቂቃ የክሪዝስቶም ንታንቢ ለመሀል ሜዳ የተጠጋ ቅጣት ምት ከባድ ሙከራዎችን ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች እጅግ ያስፈልጋቸው የነበረውን ጎል ማግኘት ግን አልቻሉም። 77ኛው ደቂቃ ላይም ከማዕዘን ምት በተነሳ ኳስ ሳሙኤል ሳኑሚ እና ባፒትስታዬ ፋዬ ያደረጉትን ለግብ የቀረበ ሙከራ ተከላካዮች ተደርበው አውጥተውባቸዋል። አስቻለው ግራማ እና መስዑድ መሀመድን ቀይረው በማስገባት በሙሉ ሀይላቸው ጫናቸው የቀጠሉት ቡናዎች ሰባት ደቂቃዎች በተጨመሩበት ጨዋታ ከኃይሌ ገ/ትንሳይ በተነሳ ኳስ መስዑድ በግንባሩ ያደረገውም ሙከራም ግብ ሳያስገኝላቸው ቀርቶ ጨዋታው ተገባዷል።

በውጤቱ ኢትዮጵያ ቡናን ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባ ጅፋር በአራት ነጥብ ያራቀው ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በግብ ልዩነት ወላይታ ድቻን በልጦ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ችሏል።