ዋልያዎቹን ለማሰልጠን ማመልከቻ ያስገቡ አሰልጣኞች ቁጥር እንደተጠበቀው አልሆነም

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ቡድን የአሰልጣኝ ለመቀጠር ያወጣው ማስታወቂያ የመጨረሻው ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ የ3 ቀናት ዕድሜ በቀረው በአሁኑ ወቅት ማመልከቻ ያስገቡት አሰልጣኞች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ ተነግሯል። 

ያለፉትን ስምንት ወራት አሰልጣኝ አልባ ሆኖ የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ይረዳው ዘንድ ከወዲሁ አሰልጣኝ ለመቅጠር መስፈርቶችን በማውጣት ከሰኔ 19 ጀምሮ የቅጥር ማስታወቂያ እንዳወጣ ይታወቃል። የቅጥር ማስታወቂያ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት አስር ቀናት በርከት ያሉ መስፈርቱን የሚያሟሉ አሰልጣኞች ማመልከቻዎቻቸውን ያስገባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ቀነ ገደቡ ሊጠናቀቅ የ3 ቀናት እድሜ በቀረው በአሁኑ ሰአት ከአምስት የማይበልጡ ስም ያላቸውና እና ሌሎችም አሰልጣኞች ማመልከቻቸውን ያስገቡ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል። ለአብነት ያህል የቀድሞ የወላይታ ድቻ እና የአሁኑ የፋሲል ከተማ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እንዲሁም በሁለት አመት የኢትዮዽያ ቆይታቸው ቅዱስ ጊዮርጊስን በተከታታይ የፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ያደረጉት ሆላንዳዊው ማርት ኑይ ማመልከቻ ካስገቡ አሰልጣኞች መካከከል ይጠቀሳሉ።

አስቀድሞ በወጣው የቅጥር መስፈት ላይ ፌዴሬሽኑ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ጥያቄዎች ማስነሳቱ የሚታወስ ሲሆን ምን አልባት የማሰልጠን ፍላጎቱ የቀዘቀዘው ፌደሬሽኑ ያወጣው መስፈርት ለብዙ አሰልጣኞች ለመወዳደር አመቺ ባለመሆኑ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል።  በቀሪዎቹ  ቀናት ማመልከቻ የሚያስገቡት አሰልጣኞች ቀድመው ካስገቡት የተለየ ነገር ከሌለው ፌዴሬሽኑ አወዳድሮ ለመቅጠር የሚቸገር በመሆኑ ለተጨማሪ ቀናት ሊያራዝም አልያም ሌላ መንገድ ሊከተል እንደሚችል ለማወቅ ችለናል።