ትውልደ ኢትዮጵያዊው ታዳጊ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ጋር የዓለም ዋንጫ የመመልከት እድል አግኝቷል

በፊፋ የ2018 ዓለም ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ፈረንሳይ እና ዩራጋይ ዓርብ ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ በፓሪስ እና አቅሪቢያዋ ከተወጣጡ ታዳጊ እግርኳስ ተጨዋቾች ጋር ይህንን የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ለመመልከት አቅደዋል፡፡ ከተጋበዙ ተጨዋቾች መካከል ደግሞ ከኢትዮጵያዊያን ቤተሰቦች የተወለደው ብሩክ ሲሳይ ይገኝበታል፡፡

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በየካቲት 2/2005 በፓሪስ አቅራቢያ የተወለደው ብሩክ በቡሎኝ ቢዮንኩር ክለብ ውስጥ በአጥቂነት እየተጫወት ይገኛል፡፡ የ13 ዓመቱ ቡሩክ ፕሬዝደንት ማክሮ በዓለም ዋንጫው ፈረንሳይ ከዩራጋይ የሚደርጉትን ጨዋታ በኤሊዜ ቤተ-መንግስት እንዲመለከት ጥሪ ከቀረበለት ተስፈኛ ታዳጊዎች መካከል አንዱ ሲሆን ተጨዋቹ እና አባቱ አቶ ሲሳይ መሃቤ እድሉን አግኝቶ ፕሬዝደንት ማክሮን የማግኘት እና የዓለም ዋንጫ ጨዋታን የመመልከት እድል በማግኘቱ ደስተኛ መሆናቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ቡሎኝ ቢዮንኩር በተለያዩ ስፖርቶች የሚሳተፍ በፓሪስ አቅራቢያ የሚገኝ ክለብ ሲሆን በእግርኳሱ በይበልጥ ለወቅቱ የፈረንሳይ ሃያል ክለብ ፓሪ ሰ ዠርማ መጋቢ በመሆን ይታወቃል፡፡ በክለቡ ውስጥ አልፈው ትልቅ ደረጃ ሊደርሱ ከቻሉ ተጨዋቾች መካከል የቀድሞ የኒውካስል ዩናይትድ የክንፍ ተጨዋች ሃቲም ቤን አርፋ እና የቀድሞ የሊቮርኖ እና ፓርማ አጥቂ አልጄሪያዊው ኤሻክ ቤልፎዲል ይጠቀሳሉ፡፡

ብሩክ በመጪው ሰኞ በስዊድን በሚዘጋጀው ጎቲያ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ከክለቡ ጋር ወደ ጎተንበርግ ያመራል፡፡ ጎቲያ ዋንጫ በዓለማችን በርካታ ቁጥር ያላቸውን የታዳጊ ቡድኖች በማሳተፍ የሚስተካከለው ውድድር የለም፡፡ የስዊድኑ ክለብ ቢኬ ሃከን በሚዘጋጀው በዚህ ውድድር ላይ ከዚህ ቀድም አሁን በህይወት በሌለው የቀድሞ ድንቅ አጥቂ አሰግድ ተስፋዬ የሚመራው አሴጋ የእግርኳስ አካዳሚ መሳተፉ ይታወሳል፡፡