ፕሪምየር ሊግ | ሲዳማ ቡና ከመውረድ ስጋት ነፃ ሲወጣ ደደቢት ከወልዲያ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ተካሂደው ደደቢት እና ወልዲያ ነጥብ ሲጋሩ ሲዳማ ቡና መከላከያን በማሸነፍ ከመውረድ ስጋት ነፃ መውጣቱን ማረጋገጥ ችሏል።

የአዲስ አበባ ስታዲየም ከሰሞኑ እየጣለ ባለው ዝናብ ሜዳው ለማጫወት ምቹ ባለመሆኑ ምክንያት ወደ ሰበታ የተቀየረው የደደቢት እና የወልዲያ ጨዋታ ግብ ሳይስተናገድበት ተጠናቋል። ጨዋታው በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይደረጋል ተብሎ ቢታሰብም ፌድሬሽኑ ግን ዛሬ ማለዳ ለክለቦች 04:00 ላይ እንደሚደረግ ባሳወቀው መሠረት ተከናውኖ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ወልዲያ ከ8 ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሳይሸነፍ ሲወጣ ደደቢት ሙሉ ለሙሉ ከመውረድ ስጋት ነፃ መሆን ችሏል።

ይርጋለም ላይ በ9:00 ሲዳማ ቡናን ከመከላከያ ያገናኘው ጨዋታ በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ባዬ ገዛኸኝ ከክለቡ በተላለፈበት ቅጣት ምክንያት አዲስ ግደይን በፊት አጥቂነት ያሰለፈው ሲዳማ ቡና አሁንም የአዲስ ጎሎች ጥገኛ መሆኑን ቀጥሏል። ተመጣጣኝ በነበረው የመጀመርያ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ሲዳማ ቡና የተሻለ የጎል እድል መፍጠር ችሏል። በ14ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ዮሀንስ ያቀበለውን ኳስ አዲስ ግደይ ቢመታትም ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ያወጣበት 18ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ወንድሜነህ ዓይናለም በቀጥታ ወደ ግብ የላካትን ኳስ አቤል ማሞ ጨርፎ የግቡን ቋሚ ነክታ ወደ ውጭ የወጣችበት ሙከራም የሚጠቀሱ ናቸው። መከላከያዎች ደግሞ በመስመር ላይ አመዝነው ሳሙኤል ታዬንና ሳሙኤል ሳሊሶን ትኩረት ያደረገ የአጨዋወት መንገድን መከተል ሲችሉ 25ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ገብረማርያም ከሳሙኤል ሳሊሶ ያገኘውን አጋጣሚ በቀላሉ ያመከናት ዕድል የምታስቆጭ ነበረች። በድጋሚ ፍፁም በግል ብቃቱ ሌላ አጋጣሚ ቢያገኝም ኳስ እና መረብ መገናኘት ሳይችሉ ሁለቱም ክለቦች ወደ መልበሻ አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ፈጣን እንቅስቃሴን ያሰቡ የሚመስሉት ሲዳማዎች 46ኛው ደቂቃ ላይ ወንድሜነህ አይናለም እና ዮሴፍ ዮሀንስ በአንድ ሁለት ቅብብል አድርገው ዮሴፍ አሾልኮ ለአዲድ ግደይ ሰጥቶት ሶስት የመከላከያ ተከላካዮችን በማለፍ አቤል ማሞን ወደ ተቀራኒ አቅጣጫ አስቶ ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ ማድረግ ችለዋል፡፡ ከግቡ በኋላ ውጤቱን አስጠብቆ ለመወጣት ጥረት ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች በመከላከያ ብልጫ ተወስዶባቸው ታይተዋል።

አቅሌሲያስ ግርማን እና ምንይሉ ወንድሙን በተጨማሪ አጥቂነት ፍፁም ገ/ማርያም ላይ ጨምረው ያስገቡት አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጫና ማሳደር ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ግን ተስኗቸዋል። በተለይ ፍፁም ገ/ማርያም በተደጋጋሚ ወደ ሳጥን ውስጥ በመግባት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርግ ተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል ፈተና ሆኖበታል። ዳዊት እስጢፋኖስ መሬት ለመረት መቶ የወጣበት እና በ79ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳሊሶ ያሻገራትን ኳስ ሳሙኤል ታዬ በግንበሩ ገጭቶ መሳይ አያኖ የያዘበት ተጠቃሽ የጦሩ ሙከራዎች ነበሩ። በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና ሙጃይድ መሀመድ እና ክፍሌ ኬአን ቀይሮ በማስገባት ውጤቱን ለማስጠበቅ ተጫውቷል። ከዚህ በተጨማሪ 82ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛሀኝ ወደ ግብ እየገፋ ገብቶ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርግ ከአቤል ማሞ ጋር ተጋጭቶ አቤል ማሞ ጉዳት በማስተናገዱ በይድነቃቸው ኪዳኔ ተተክቶ ወጥትቷል። ግብ ጠባቂው በቀጥታ ወደ ሆስፒታልም አምርቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ጨዋታው ለሲዳማ ቡና ሁለተኛ ተከታታይ ድል ሆኖ ክለቡ ለከርሞው በሊጉ መቆየቱን ያረጋገጠበትም ሆኗል።