የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በደደቢት ቻምፒዮንነት ተጠናቀቀ

የ2010 የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲከናወኑ ቻምፒዮኑ ደደቢት ዋንጫውን ተረክቧል።

08:00 ላይ ጌዴኦ ዲላን በአአ ስታድየም ያስተናገደው ደደቢት 3-1 በማሸነፍ በድል የውድድር ዘመኑን አጠናቋል። ዲላዎች በሁለት ረድፍ ተሰልፈው በመቆም ለደደቢት የክብር አቀባበል በማድረግ በጀመረው ጨዋታ ጎሎች መቆጠር የጀመሩት ገና በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ነበር። በ1ኛው ደቂቃ ትዕግስት ዘውዴ ከመስመር ያሻገረችውን ኳስ የዲላዋ ተከላካይ መንደሪን አንድሁን በራሷ መረብ ላይ አሳርፋለች። ሆኖም የደደቢት መሪነት ከአራት ደቂቃ አልዘለለም። ሳራ ነብሶ በጥሩ ሁኔታ አንድ ተከላካይ በማለፍ አስቆጥራ ዲላን አቻ አድርጋለች። ከ3 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ከግቡ የቀኝ አቅጣጫ የመታችው ኳስ ከመረብ አርፎ ደደቢት በድጋሚ መሪ መሆን ችሏል።

ከጎሎቹ በኋላ ጨዋታው የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የተስተዋለበት ሲሆን ለጎል የቀረቡ የግብ ሙከራዎችም ሳንመለከት ዘልቋል። በ82ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ቤዛ ተስፋዬ ያመቻችላትን ኳስ ብርቱካን በጥሩ አጨራረስ የደደቢትን አሸናፊነት ያስተማመነች ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በደደቢት 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። አመቱን ሙሉ ሳይሸነፍ የዘለቀው ደደቢት ድሉን ተከትሎ ከተከታዩ ንግድ ባንክ በ3 ነጥቦች ከፍ በማለት በ44 ነጥቦች ለተከታታይ 3ኛ አመት በአጠቃላይ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ ቻምፒዮን ሲሆን ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ከቡድኑ ጋር ያልነበረችው ሎዛ አበራ በ17 ጎሎች የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን ክብር ለ4ኛ ተከታታይ አመት አሳክታለች። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባላት ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ ቡድኖች እንደየደረጃቸው የሜዳልያ ሽልማት ሲያበረክቱ የደደቢቷ አምበል ኤደን ሽፈራው ከፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ኮ/ል አወል አብዱራሂም ዋንጫውን ተቀብላ የመርሐ ግብሩ ፍፃሜ ሆኗል። 

በሌሎች የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሁለተኝነት ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅዱስ ጊዮርጊስን በህይወት ደንጊሶ (2)፣ ብዙነሽ ሲሳይ እና ረሒማ ዘርጋው ጎሎች 4-1 ሲረታ መከላከያ አዳማ ከተማን 2-1 በማሸነፍ በ3ኛነት አጠናቋል። ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከ ኤሌክትሪክ 2-2 ፤ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ከሀዋሳ ከተማ ያለጎል አቻ የተለያዩበት ጨዋታዎች ሌሎች ዛሬ የተደረጉ ናቸው። 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሲዳማ ቡና ከሊጉ የወረዱ ቡድኖች ሲሆኑ የ2ኛ ዲቪዝዮን ቻምፒዮኑ ጥረት ኮርፖሬትን ጨምሮ አርባምንጭ ከተማ፣ አአ ከተማ እና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ያደጉ ቡድኖች ናቸው።