ሪፖርት| ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን አስጠብቋል

በ29ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አዳማ አቅንቶ ጨዋታውን በአቻ ውጤት አጠናቋል። ከፍተኛ ግምት ተሰቶት በነበረው የአዳማ ከተማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር የተስተዋለበት ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ከጨዋታው ነጥብ ለማግኘት ሲጥሩ ታይቷል። 

በከፍተኛ የደጋፊ ቁጥር ታጅቦ በተከናወነው ጨዋታ አዳማ ከተማዎች በ4-2-3-1 ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ በ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን የጨዋታዎቹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ባለሜዳዎቹ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ሲሞክሩ ተጋባዦቹ ደግሞ ከቆሙ እና ከተሻጋሪ ኳሶች የግብ አጋጣሚዎችን ፈጥረው ገና በጊዜ ቀዳሚ ለመሆን ሲሞክሩ ታይቷል። የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ በኃይሉ አሰፋ አማካኝነት የተገኘ ሲሆን በኃይሉ ከግራ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክሮት ግብ ጠባቂው ጃኮ ፔንዜ ተቆጣጥሮታል። ከስድስት ደቂቃዎች በኃላ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻለ የነበሩት አዳማዎች በበረከት ደስታ አማካኝነት የመጀመሪያ ሙከራ አድርገው ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ የተመታችው ኳስ ኢላማዋን ስታ ወደ ውጪ ወታለች።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ሪትም የገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጨዋታው ሲጀመር በኃይሉ አሰፋን በቀኝ ኦዝቫልዶ ታቫሬስን ደግሞ በግራ መስመር አሰልፈው ተሻጋሪ ኳሶችን ለአሜ መሃመድ ለመጣል ሲሞክሩ ቆይተው በየ15 እና 20 ደቂቃው የሁለቱ ተጨዋቾችን ቦታ በማቀያየር የተጋጣሚን የመከላከል አደረጃጀት ጥሶ ለመግባት ጥረዋል። በ19ኛው ደቂቃ ላይ መሃሪ መና ለአሜ መሐመድ ግሩም ኳስ አሻግሮለት አሜ ኳሷን በውስጥ እግሩ መትቶ ለማግባት ሲሞክር ሙሉ ለሙሉ ሳያገኛት ያመከናት ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ ነበረች። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አዳማዎች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ጊዮርጊሶች የግብ ክልል በመድረስ በረከት ደስታ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት የሞከራት ኳስ ተቆርጣ ወደ ውጪ ወጥታለች። በመጀመሪያው አጋማሽ በአሜ አማካኝነት ብቻ የግብ እድል ሲፈጥሩ የቆዩት ጊዮርጊሶች አሁንም በ28ኛው ደቂቃም በአሜ አማካኝነት ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝተው አሜ ኳሷን ወደ ግብ ሲመታት በኃይል ባለመሆኑ በቀላሉ ግብ ጠባቂው ጃኮ ተቆጣጥሮታል።

ከ30ኛው ደቂቃ በኃላ ሁለቱም ቡድኖች ተረጋግተው ኳስን በመቀባበል ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን ከሁለቱም ቡድኖች ፍላጎት አንፃር ኳሶችን ቶሎ ቶሎ ሲነጣጠቁ ተስተውሏል። እንደ አጀማመሩ ፉክክሩ ያልቀጠለበት የመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ምንም የግብ ሙከራ ሳያስተናግድ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ባለሜዳዎቹ አዳማ ከተማዎች ተጭነው ለመጫወት ሲሞክሩ በተለይ በአንድ ሁለት ቅብብል ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርሱ ተስተውሏል። አዳማዎች ምንም እንኳን ወደ ጊዮርጊሶች የግብ ክልል በቀላሉ ለመድረስ ቢችሉም የጠሩ የግብ እድሎችን ግን እምብዛም ሲፈጥሩ አልታየም። በተቃራኒው የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ተቀዛቅዘው የታዩት ጊዮርጊሶች ተጋጣሚያቸው ጫናዎችን እያሳደረባቸው መሆኑ ተከላክለው በመልሶ ማጥቃት እንዲጫወቱ አስገድዷቸዋል። በዚሁ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጊዮርጊሶች ተጋጣሚያቸው ለማጥቃት መውጣቱን ተገንዝበው ረጅም ኳስ ለበኃይሉ ሲልኩለት የአዳማዎች የመሃል መስመር ተከላካይ ምኞት ደበበ ኳሷን ለማስቀረት በእጁ በመንካቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣ ሲሆን ኳሷ ብታልፍ ቡድኑ ላይ አደጋ ልትፈጥር የምትችል አጋጣሚ ነበረች።
ከቀይ ካርዱ በኃላ አዳማ ከነማዎች በ4-4-1 አሰላለፍ ብልቻ ሹራን አስወጥተው ተስፋዬ በቀለን በማስገባት ከነዓን ማርክነህን ወደ ግራ በማስወጣት የተጫወቱ ሲሆን ተጋጣሚያቸው ላይ ጫና ማሳደራቸውን ትተው ወደ ኃላ አፈግፍገው ለመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት  ሲሞክሩ ታይቷል። በ59ኛው ደቂቃ ከጃኮ ፔንዜ የተመታውን ኳስ የጊዮርጊስ ተጨዋቾች ተዘናግተው በቆሙበት ሰዓት ከነዓን ከተከላካዮች ጀርባ በመሮጥ ኳሷን አግኝቷት ወደ ግብ ሲሞክራት ሮበርት ኦዶንካራ በአስገራሚ ሁኔታ ያወጣበት በአዳማ በኩል በጨዋታው ከተፈጠሩ አጋጣሚዎች ሁሉ የላቀች አስቆጪ እድል ነበረች።

ቀይ ካርዱ የጠቀማቸው የሚመስሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቁጥር ብልጫ ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ በመሆናቸው ጫናዎችን በማድረግ በተለይ ከዚህ በፊት በሚታወቁበት የጨዋታ ዘይቤ ኳስን ወደ መስመር በማውጣት ሙከራዎችን በመስመር በኩል ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውሏል። በ64ኛው ደቂቃ መሃሪ መና ከግራ መስመር የተገኘውን ኳስ ከማሻማት ይልቅ በቀጥታ ወደ ግብ ኳሳን በመምታት ያልታሰበ የግብ ማግባት አጋጣሚ ፈጥሮ ጃኮ እንደምንም ወደ ውጪ አውጥቷታል። አሁንም ጫናዎችን ማድረጋቸውን የቀጠሉት ጊዮርጊሶች በ70ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ የቡድኑ አምበል ናትናኤል ዘለቀ በግንባሩ ሞክሮት የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ቡድኑን መሪ ልታደርግ የምትችል ሌላ አስቆጪ እድል ነበረች።


በአዳማዎች በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ከነዓን ማርክነህ የቡድኑን የአማካይ እና የአጥቂ መስመር በሚገባ ሲያገናኝ የነበረ ቢሆንም ከቀይ ካርዱ በኃላ ወደ ግራ መስመር በመውጥቱ ዳዋ ኳሶችን በሚገባ ሲያገኝ አልነበረም። ሰዓት እየገፋ በሄደ ቁጥር ጎል ለማስቆጠር ተነሳስተው የነበሩት ጊዮርጊሶች ወደ ፊት በመውጣት ለመጫወት ሲሞክሩ አዳማ ከተማዎች ኳሶችን እየቀሙ በረጅሙ በመምታት ለዳዋ በመጣል እደን ለመፍጠር ጥረዋል። በዚሁ የጨዋታ ሁኔታ በጭማሪው ሰዓት ዳዋ የመጨረሻ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝቶ ወደ ግብነት ለመቀየር ኳሷን በሚገባ ሞክሯት ሮበርት አወጣበት እንጂ ባለቀ ሰዓት ያልታሰበ እድል አግኝተው ነበር።


የአሰልጣኝ አስተያየት:

ተገኔ ነጋሽ – አዳማ ከተማ

ጨዋታው ጥሩ ነበር። ሁለታችንም ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። ነጥባችን ከፍ እንዲል እንፈልግ ነበር። ያ እንዲሆን ደግሞ በከፍተኛ ትኩረት ተጫውተናል። ለመጨረሻዎቹ 40 ደቂቃዎች በ10 ተጫዋች ነው የተጫወትነው። ይሄ ደግሞ ተከላክለን በህብረት ጫናዎችን ቀንሰን እንድንጫወት አድርጎናል።

ቫዝ ፒንቶ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቡድኔ ዛሬ ጥሩ ነበር። በጨዋታው ብዙ  የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረን አንዱንም ሳንጠቀምበት ወጥተናል። ተጫዋቾቼ ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል፤ የሚችሉትንም አድርገዋል በዚህ ደግሞ ደስተኛ ነኝ። ተጋጣሚያችን ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች ነበሯቸው። ሜዳ ላይ የሚያሳዩት ታጋይነትም ጥሩ ነው። ቀጣይ ያለብን የሃዋሳ ጨዋታ ላይ ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንሞክራለን። በዛሬው ጨዋታ የነበሩብንን የግብ ማግባት ክፍተቶች በማረም ተሻሽለን እንቀርባለን።