ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ እና አርባ ምንጭ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

በ29ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በድሬዳዋ ስታዲየም የተካሄደው የተካሄደው የድሬዳዋ ከተማ እና አርባ ምንጭ ከተማ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ድሬዳዋ ከተማ በ28ኛው ሳምንት አዲስ አባባ ላይ ከቡና ጋር ነጥብ ከተጋራው የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ምንም ቅያሬ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ሲገባ ሀዋሳ ከተማን ሜዳው ላይ አስተናግዶ ነጥብ የተጋራው አርባምንጭ በበኩሉ ፀጋዬ አበራን በበረከት አዲሱ ቀይሮ በመጀመሪያው አሰላለፍ ውስጥ በማካተት ወደ ሜዳ ገብቷል።

ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄ በተሞላ ሁኔታ ኳስ ይዞ ለመጫወት ጥረት ስያደርጉ የተስተዋለ ሲሆን ድሬድዋ ከተማዎች ወደ ጎል ለመድረስ የተሻሉ ነበሩ። በ10ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳንኤል ከመስመር ያሻማው ኳስ ሀብታሙ ወልዴ መትቶ ወደ ወጪ ያወጣት ኳስ የመጀመሪያ ጥሩ የሚባል የጎል ሙከራ ነበረች። በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ግብ ሲደርሱ የነበሩት  አርባምንጮች በ16ኛው ደቂቃ በረከት አዲሱ ያሻማውን ኳስ እንዳለ ከበደ ወደ ግብ ቀይሮ ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ድሬዎች ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን በ20ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ወልዴ በጭንቅላት ለዳኛቸው በቀለ ያቀበለውን ኳስ ዳኛቸው በጭንቅላት በመግጨት የአርባምንጩ ግብ ጠባቂ ጽዮን መርዕድ አድኖታል። በ25ኛው ደቂቃ ላይ ኢማኑኤል ላሪያ ከመሀል ያሻማዋውን ኳስ ዮሴፍ ዳሙዬ ወደ ጎል በቀጥታ መትቶ ጽዮን በቀላሉ ተቆጣጥሮታል። በ36ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ዳሙዬ ከመስመር ያሻገራትን ኳስ ወሰኑ ማዜ ወደ ጎል መትቶ ወደ ውጪ ሲወጣ በ40ኛው ደቂቃ አህመድ ረሺድ ከመስመር በጥሩ ሁኔታ ያሻማውን ኳስ አጥቂው ሀብታሙ ወልዴ በጭንቅላት ገጭቶ በጽዮን ተይዞበታል። የአቻነት ጎል ፍለጋ ተጭነው በመጫወት የቀጠሉት ድሬዳዋዎች በ43ኛው ደቂቃ በሀብታሙ ወልዴ አማካኝነት ለጎል የቀረብች ሙከራ ቢያደርጉም ጎል ሳያስቆጥሩ የመጀመሪያው አጋማሽ በአርባምንጭ መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ የአቻነት ጎል ፍለጋ መጫናቸውን ሲቀጥሉ አርባምንጮች መሪነታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት ያለመ የመከላከል እንቅስቃሴ አድርገዋል። በ48ኛው ደቂቃ ላይ ዘነበ ከበደ በመስመር ገፍቶ ያመጣትን ኳስ ራሱ አክርሮ በመምታት ለጥቂት ወደ ውጪ የውጣችው ኳስ ከእረፍት መልስ የመጀምሪያ ሙከራ ስትሆን 56ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን ናስር በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎል የላካት የቅጣት ምት ኳስ በተከላካዮቹ ብትጨረፍም ጽዮን በቡጢ አውጥቷላል። በ64ኛው ደቂቃ ደግሞ አህመድ ረሺድ ከመስመር ይዞ የገባው ኳስ በአለልኝ ተጨርፋ ወደ  ውጪ የወጣችው እና በ72ኛው ደቂቃ ዘነበ ከበደ ከመስመር ያሻማውን ኳስ  ሀብታሙ ወልዴ ሞክሮ ወደ ውጪ ያወጣት ኳስ ሌላው የባለሜዳዎቹ ሙከራዎች ናቸው 

አሁንም ተጭነው በመጫወት ጎል ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉት ባለሜዳዎቹ  85ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ረሽድ አደራጅቶ ያመጣውን ኳስ በማሻማት ዮሴፍ ዳሙዬ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ ሲያድንበት 90ኛው ደቂቃ ላይ ዘነበ ከበደ ያሻማውን ኳስ በረከት ይስሀቅ በጭንቅላቱ በመግጨት ባለሜዳዎቹን አቻ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል።  

በጎሉ መቆጠር ቅፅበት ከደጋፊ ወደ አርባምንጭ ተጠባባቂዎች የውሃ ፕላስቲክ መወርወሩን ተከትሎ የቡድኑ አባላት ወደ ሜዳ በመግባት እንደማይጫወቱ በመግለፅ ለ18 ያህል ደቂቃዎች ጨዋታው ለመቋረጥ ተገዷል። የፀጥታ ኃይሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ በመግለፁም ሁኔታው ከተረጋጋ በኋላ በድጋሚ ጨዋታው ተጀምሮ በተጨማሪ ሰዓት ላይ አህመድ ረሺድ ያሻማውን ኳስ ሀብታሙ ወልዴ ወደ ግብ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ የመጨረሻ የጎል ሙከራ ሆኖ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።