አብርሃም መብራቱ ለዋልያዎቹ አሰልጣኝነት ሰፊ እድል አላቸው

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ለመቅጠር  ከሰሞኑ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ፌዴሬሽኑ አብርሀም መብራቱን ቀጣዩ አሰልጣኝ ለማድረግ መቃረቡ ተነግሯል። 

አስቀድሞ ያወጣው የአሰልጣኝ ቅጥር መስፈርት በማስቀረት የቴክኒክ ኮሚቴው አምስት አሰልጣኞችን ለይቶ በመምረጥ አወዳድሮ ለመቅጠር ከወሰነ በኋላ የጅማ አባ ጅፋሩ አሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌ፣ የወልዋሎ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም፣ የመከላከያ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ፣ የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና የየመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱን ቃለ መጠይቅ በማድረግ እንዳጠናቀቀ ታውቋል።

ቴክኒክ ኮሚቴው የአሰልጣኞቹን ቃለ መጠይቅ ካጠናቀቀ በኋላ ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የቀረበለት ሪፖርት መሰረት በማድረግ ከመረመረ በኋላ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን ለመጨረሻ እጩ አሰልጣኝነት ከለየ በኋላ በድምፅ ብልጫ እንዲለይ ወስነው አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ቀጣይ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው እንዲያገለግሉ ስድስት ለአምስት በሆነ የድምፅ ብልጫ ተመርጠዋል።

ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ከየመን ብሔራዊ ቡድን ጋር እንደተለያዩ ሪፖርቶች እየወጡ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት በቃለ-መጠይቁ ወቅት በአሰልጣኙ በኩል የቀረቡትን ቅድመ ሁኔታዎች ፌዴሬሽኑ የሚያሟላ ከሆነ በቅርቡ ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የቅጥሩ ሁኔታ ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል። ድርድሩ አጥጋቢ ውጤት የማያስገኝ ከሆነ ደግሞ በሁለተኛ አማራጭነት የተያዙት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቀጣዩ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።