አጫጭር መረጃዎች

ረቡዕ ሐምሌ 4 ቀን 2010


የጥናት ኮሚቴ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከሁለት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መዋቅራዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ዙርያ ጥናት የሚያደርግ ኮሚቴ አቋቁሞ እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚታወስ ነው። በፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ስር 3 አባላት የተካተቱበት ኮሚቴው ጥልቅ ጥናት ለማድረግ በቂ ስለመሆኑ ፌዴሬሽኑ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ጥያቄ ሲነሳበት የነበረ ሲሆን ምሁራንን ያካተተ እንዲሆንም አስተያየት መሰጠቱ ይታወሳል። በዚህም መሠረት ፌዴሬሽኑ ተጨማሪ ግለሰቦችን በኮሚቴው አካቷል። ዶ/ር ተረፈ (ጅማ ዩኒቨርሲቲ)፣ ዶ/ር አመንሲሳ ከበደ (ኢ/ወ/ስ አካዳሚ)፣ ዶ/ር ተገኔ (ከኮተቤ ሜ/ዩ) እና አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ግለሰብ ከአአ ዩኒቨርሲቲ መካተታቸው ታውቋል።

የጥናት ቡድኑ ስራውን ከጀመረ 10 ቀናት ያስቆጠረ ሲሆን በዚህ ወር የጥናት ሰነዱን ለፌዴሬሽኑ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።


የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 30ኛ ሳምንት መርሐ ግብር

አርብ ሐምሌ 6 ቀን 2010

04:00 መከላከያ ከ ደደቢት (ሰበታ)
08:00 ኢትዮጵያ ቡና ከ መቐለ ከተማ (አአ)

ቅዳሜ ሐምሌ 7 ቀን 2010

09:00 ወልዲያ ከ ወላይታ ድቻ (ወልዲያ)
09:00 ወልዋሎ ከ ድሬዳዋ ከተማ (ዓዲግራት)
09:00 ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሲዳማ ቡና (ሰበታ)
09:00 አርባምንጭ ከ ፋሲል ከተማ (አርባምንጭ)

እሁድ ሐምሌ 8 ቀን 2010

08:00 ጅማ አባጅፋር ከ አዳማ ከተማ (ጅማ)
08:00 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዋሳ ከተማ (አአ)


ቅሬታ

በ30ኛ ሳምንት በመርሐ ግብር አወጣጥ ዙርያ መከላከያ ቅሬታውን አሰምቷል። ከደደቢት ጋር ሰበታ ላይ በ4:00 የሚጫወተው መከላከያ የሰበተመ ሜዳ አመቺ አለመሆኑን በመግለፅ ቅሬታውን ገልጿል።


ወልዲያ

ወልዲያ ከቅጣቶች በኋላ የመጀመርያ የሜዳ ጨዋታውን ቅዳሜ ወላይታ ድቻን በማስተናገድ ያከናውናል። ሆኖም የቡድኑ ተጫዋቾች ወደ ስፍራው ተጉዘው መጫወት እንደማይፈልጉ ሲገልፁ ክለቡ ደግሞ ጨዋታው በሜዳው እንደሚከናወን አስታውቋል። የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገረመው ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን ብለዋል። ” እኛ የምንፈልገውም ሆነ መርሀ ግብሩ የሚያዘው ወልዲያ ላይ ጨዋታው እንዲከናወን ነው። አሁን ላይ እየተሰማ ያለው ነገር ደግሞ ተጫዋቹች ወደ ወልዲያ ተመልሰው መጫወት እንደማይፈልጉ ነው። ይህ ነገር ቡድኑን ፎርፊ እንደሚያሰጥ ይታወቃል። በዚህ ሳቢያም በሌሎች ቡድኖች ላይ ነጥብ ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ግልፅ ነው። ሐምሌ 4 (አስተያየታቸውን የሰጡት ትላንት ምሽት ነው) ቦርዱ ስብሰባ ለማድረግ አስቧል።”


አንደኛ ሊግ

የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የምድብ ጨዋታዎች ዚህ ሳምንት ይጠናቀቃሉ። በምድብ ሠ ሀዲያ ሌሞ ከ ቡሌ ሆራ፣ ጎፋ ባሪንቼ ከ ሺንሺቾ ከተማ ነገ 04፡00 በሚያደርጓቸው ጨዋታዎችም ከዚህ ምድብ የሚያልፈው ሶሰቸኛ ቡድን ይለያል። ጨወመታውን የጨረሰው ጋሞ ጨንቻ በ31 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ 29 ነጥብ ያላቸው ሺንሺቾ እና ቡሌ ሆራ ተጋጣሚዎቻቸውን ካሸነፉ ሶስተኛ የመሆን እድል አላቸው።

እስካሁን ወደ ማጠቃለያ ውድድሩ ማለፋቸውን ቡድኖች የሚከተሉት ናቸው፡-

ቱሉ ቦሎ፣ አራዳ፣ አሶሳ ከተማ፣ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ፣ ሞጆ ከተማ፣ ገላን ከተማ፣ ራያ አዘቦ፣ አምባ ጊዮርጊስ፣ ዳሞት ከተማ፣ ጎጃም ደብረማርቆስ፣ ናኖ ሁርቡ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ወላይታ ሶዶ፣ አርሲ ነገሌ

አዳማ ላይ ለማካሄድ የታሰበው የማጠቃለያ ውድድር ላይ 16 ክለቦች እንደሚካፈሉ ሲጠበቅ 14 ቡድኖች ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። አንደኛው አላፊ ከምድብ ሠ ነገ ሲታወቅ አሰራሩ ግልፅ ያልሆነው የጥሩ 4ኛ ጉዳይ እስካሁን አለየለትም።


ሴቶች ብሔራዊ ቡድን

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን መቀመጫውን አዳማ በማድረግ 22 ተጫዋቾችን ይዞ ከሰኞ ጀምሮ የሴካፋ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል። ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣዩቹ ቀናትም ዝግጅቱን የሚቀጥል ሲሆን ሐምሌ 10 ወደ አስተናጋጇ ሩዋንዳ የሚያመራ ይሆናል። ሐምሌ 14 ደግሞ የመጀመርያ ጨዋታውን ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያደርግ ይሆናል።


እጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት

የኢትዮጵያ ከ17 እና 20 ዓመት በታች የማጠቃለያ ውድድሮች የእጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት ዛሬ በባቱ ከተማ ይከናወናል። በሁለቱም የእድሜ እርከኖች 10 ቡድኖች የሚካፈሉበት ውድድር የ17 ዓመት በታች ነገ ሲጀመር የ20 ዓመት በታች ከነገ በስቲያ የሚጀመር ይሆናል።


ከፍተኛ ሊግ

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ከነገ በስቲያ (አርብ) ወሳኝ የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ይከናወናሉ። መሪው ባህርዳር ከተማ የካ ክፍለከተማን ሲያስተናግድ አክሱም ላይ አክሱም ከተማ ከ አአ ከተማ፣ አአ ላይ ደሴ ከተማ ከ ሽረ እንዳስላሴ በተመሳሳይ 4:00 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።