ከ20 ዓመት በታች የማጠቃለያ ውድድር ዛሬ ተጀመረ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ዛሬ በባቱ ከተማ ሲጀመር በሁለት ምድቦች አራት ጨዋታዎች ተደርገው አአ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ማሸነፍ ችለዋል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና የፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ በተገኙበት በባቱ ስታድየም እና ሼር ኢትዮጵያ ስታድየም እኩል 08:00 ላይ በሁለት ጨዋታዎች ሲከፈት በምድብ ሀ ባቱ ስታድየም ላይ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚን የገጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አሸንፏል። በከፊል ገላጣ የሆነው የሜዳ ክፍል ለተጫዋቾቹ ፈታኝ የነበረ ሲሆን ለእንቅስቃሴ ከማስቸገሩ ባሻገር በተደጋጋሚ ሚዛናቸውን ሲስቱ እና ጉዳት ሲያስተናግዱ ተስተውሏል።

የተቀዛቀዘ ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት ጨዋታ በ90 ደቂቃ ውስጥ እጅግ ጥቂት የጎል አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል። በ4ኛው ደቂቃ የጊዮርጊሱ አቡበከር ሙራድ ከርቀት አክሮ የመታውና በግቡ አናት የወጣበት ሙከራ ብቸኛው በመጀመርያ አጋማሽ የሚጠቀስ አጋጣሚ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ 51ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ስነወርቅ ጌታቸው በጎሉ ግራ በኩል ከጠበበ አንግል ግሩም ጎል አስቆጥሮ ጊዮርጊስን ወሳኝ ሶሰት ነጥብ አስጨብጧል። ከጎሉ በኋላ ጥሩነሽ ዲባባዎች ለአቻነት ተጭነው መጫወት ችለው ነበር። በተለይም በ90ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ፉአድ ኢብራሂም በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው ተመስገን ዮሀንስ ያወጣበት የሚጠቀስ ነበር። 
ከምድብ ለ በተመሳሳይ 8 ሰዓት ሼር ኢትዮጵያ ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ መድንን የገጠመው አዲስ አበባ ከተማ በመሐመድ ሙስጠፋ ብቸኛ ጎል 1-0 አሸንፏል። 

10:00 ላይ በባቱ ስታድየም ሀዋሳ ከተማ ከ መከላከያ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ይህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ከተካሄደው የተሻለ እንቅስቃሴ የታየበት ቢሆንም በግብ ሙከራዎች መታጀብ አልቻለም። በ37ኛው ደቂቃ በሀዌሳ የግብ ክልል ኳስ በእጅ መነካቱን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሰለሞን ሙላው በአግባቡ ተጠቅሞ መከላከያን መሪ እስኪያደርግ ድረስም የግብ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ አልተስተዋለም። 
በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያዎች በቁጥር አንሰውም ቢሆን በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር ሲሞክሩ ቶሎ ቶሎ ኳሶችን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመላክ የአቻነት ግብ ለማግኘት ሲጥሩ የነበሩት ሀዋሳዎች በ75ኛው ደቂቃ ያሬድ መሐመድ ከሳጥኑ አቅራቢያ በግራ በኩል አክርሮ በመምታት ባስቆጠረው ግሩም ጎል አቻ መውጣት ችለዋል። 

በተመሳሳይ 10:00 ላይ በምድብ ለ ኢትዮጵያ ቡና ፍፁም ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ታግዞ ወላይታ ድቻን 2-1 አሸንፏል። 

የ20 ዓመት ውድድሩ ነገ እረፍት ሲሆን ቅዳሜ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ይከናወናሉ።

ምድብ ሀ

03:00 ደደቢት ከ ሀዋሳ ከተማ (ባቱ)

05:00 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ (ባቱ)

ምድብ ለ

03:00 ድሬዳዋ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ (ሼር)

05:00 ኢትዮጵያ መድን ከ ኢትዮጵያ ቡና (ሼር)

ነገ የ17 ዓመት በታች ማጠቃለያ ውድድር የሚጀምር ሲሆን አራት ጨዋታዎችም ረፋድ ላይ ይከናወናሉ።

ምድብ ሀ

03:00 ወላይታ ድቻ ከ አፍሮ ፅዮን (ባቱ)

05:00 ወጣቶች አካዳሚ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ባቱ)

ምድብ ለ

03:00 ማራቶን ከ ሀዋሳ ከተማ (ሼር)

05:00 አዳማ ከተማ ከ መከላከያ (ሼር)