ፕሪምየር ሊግ| ኢትዮጵያ ቡና 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 30ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ አዲስ አበባ ላይ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ተጀምሯል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት በሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ድል ቀንቷቸዋል፡፡ መቐለ ከተማን 3-1 የረታው ቡና ሊጉን ሶስተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ ስርዓት አልበኝነት አሁንም የስታድየሞቻችን ችግር መሆኑን ቀጥሏል።

መከላከያ 2-3 ደደቢት

መከላከያ እና ደደቢት ያደረጉት ጨዋታ አምስት ግቦች ተስናግደውበት በሰማያዊዎቹ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ 4፡00 በተጀመረው ጨዋታ በርከት ያሉ የግብ እድሎች የተፈጠሩበት ሆኖ ሲያልፍ በ13ኛው ደቂቃ ሰለሞን ሐብቴ አክርሮ የመታው ኳስ የመከላከያው ተከላካይ አወል አብደላ ንክኪ ታክሎበት ደደቢትን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ተቆጥሯል፡፡ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጦሮቹ በተደጋጋሚ ወደ ደደቢት የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ግብ ለማስቆጠር ግን ተቸግረው ተስተውሏል፡፡ ዳዊት እስጢፋኖስ፣ ሳሙኤል ታዬ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በመከላከያ በኩል ማድረግ ችለዋል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ አቤል ያለው ላይ በሳጥኑ ውስጥ የተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ መቶ የደደቢትን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡

ከእረፍት መልስ መከላከያ ይበልጥ ጫና ፈጥሮ ሲጫወት ደደቢቶች በመከላከሉ ተጠምደው ታይተዋል፡፡ ወደ ደደቢት ግብ ክልል የተላከን ኳስ ለማውጣት ተከላካዮች ሲጥሩ የግብ አግዳሚ ሲገጭባቸው፤ ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት የተሻ ግዛውን ሙከራ አምክኗል፡፡ ሰለሞን የመከላከያውን ግብ ጠባቂ አቤል ማሞን አልፎ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ አቤል እንደምንም ግብ ከመሆን የታደገው ደግሞ በደደቢት በኩል የታየ ሙከራ ሲሆን በ79ኛው ደቂቃ ሰለሞን ሶስተኛውን የደደቢት ግብ በማራኪ ሁኔታ አስቆጥሯል፡፡ ጦሮቹ በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ የፈጠሩት ጫና ፍሬ አፍርቶ በአዲስ ተስፋዬ ሁለት ግቦች የግብ ልዩነቱን ቢያጠቡም ከመሸነፍ ሳይድኑ ደደቢት ሙሉ ሶስት ነጥብ በማግኘት ሊጉን ደምድሟል፡፡ ደደቢት በ41 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ መከላከያ በ35 ነጥብ በነበረበት 10 ደረጃ ላይ ረግቷል፡፡


ኢትዮጵያ ቡና 3-1 መቐለ ከተማ

ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ሶስት ግቦች መቐለ ከተማን ማሸነፍ ችሏል፡፡ ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ኤልያስ ማሞ፣ አስናቀ ሞገስ እና ጋቶች ፓኖም ለቡናው አምበል መስዑድ መሐመድ ስጦታ አበርክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በሂሳባዊ ስሌት የሊጉ ዋንጫን የማንሳት እድል በነበረው መቐለ ላይ ግብ ለማስቆጠር 3 ደቂቃዎች ብቻ ሲፈጅበት አስናቀ ሞገስ ከሳጥኑ ውስጥ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ መቶ በማስቆጠር ቡና መሪ መሆን ችሏል፡፡ የባለሜዳው ክለብ ጫና ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር እየጨመረ መጥቶ በ15ኛው ደቂቃ ሚኪያስ መኮንን አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ እያሱ ታምሩ አስቆጥሮ መሪነቱን ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡ ለዚች ግብ መገኘት ባፕቲስት ፋዬ ቁልፍ ሚናን ተጫውቷል፡፡ እያሱ ከአምስት ደቂቃዎች በኃላም በግንባሩ ገጭቶ የሞከረው ኳስ የግቡ ቋሚ መልሶበታል፡፡

በጨዋታው 30ኛ ደቂቃ ላይ የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች መካከል ረብሻ ተፈጥሯል፡፡ በ2010 በርከት ያሉ የደጋፊ ረብሻዎች የተነሱበት ፕሪምየር ሊጉ ዛሬም አሳዛኝ ክስተትን አስተናግዶ አልፏል፡፡ የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች ቁሶችን ሲወረውሩ የታየ ሲሆን በዚህም የተነሳ የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናን ተደጋጋሚ ጫናን መቋቋም ያልቻለው የእንግዳው ክለብ የተከላካይ መስመር በአጋማሹ መገባደጃ ላይ ሶስተኛ ግብ አስተናግዷል፡፡ መስዑድ ያገኘውን እድል በአግባቡ ተጠቅሞ የባለሜዳውን መሪነት አጠናክሯል፡፡

ከእረፍት መልስ በንፅፅር መቐለዎች በማጥቃቱ ረገድ ተሻሽለው ቀርበዋል፡፡ በ64ኛው ደቂቃ ጋቶች የቀድሞ ክለቡ ላይ ያስቆጠረው ግብም ለመቐለ ተስፋን የሰጠ ነበር፡፡ ከዚች ግብ መገኘት በኃላ ካርሎስ ዳምጠው ያገኘውን እድል ቢሞክርም ዩጋንዳዊው ክሪዝስቶም ንታምቢ አውጥቶበታል፡፡ ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ድሉን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ተጋጣሚው መቐለ ከተማን በመብለጥ በ50 ነጥብ የነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ መቐለ ከተማ በመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ድንቅ ጉዞ በማድረግ በ49 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋቾች እና የአሰልጣን ቡድን አባላት የነሃስ ሜዳሊያ ሽልማታቸውን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና ምክትል ፕሬዝደንት ኮሎኔል አውል አብዱራሂም እጅ ተቀብለዋል፡፡