ኢትዮጵያ ቡና ከሁለት ተጫዋቾቹ ጋር በስምምነት ተለያየ

ዘንድሮ ለኢትዮጵያ ቡና ፊርማቸውን ካኖሩ ተጫዋቾች መካከል የመስመር ተከላካዮቹ ሮቤል አስራት እና አለማየሁ ሙለታ ከክለቡ ጋር በስምምነት መለያየታቸው ታዉቋል።

ሮቤል አስራት ጅማ አባጅፋር ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባ ካስቻሉ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረ ሲሆን ወደ ኢትዮዽያ ቡና ከመጣ በኋላ በተወሰኑ ጨዋታዎች ካልሆነ በቀር በአመዛኙን ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ እድል ሳያገኝ ከቡድኑ ጋር ሲለያይ አለማየሁ ሙለታ በበኩሉ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ኢትዮዽያ ቡና ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ከጉዳት ጋር በተያያዘ በርከት ባሉ ጨዋታዎች ላይ መጫወት አለመቻሉን ተከትሎ ከቡድኑ ጋር የመለያየታቸው እርግጥ ሆኗል ።

የ2010 የውድድር አመት 3ኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ኢትዮዽያ ቡና ለሚቀጥለው የውድድር አመት በተሻለ ራሱን አጠናክሮ ለመቅረብ ከወዲሁ የዝውውር እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት ለመሳተፍ እንደሚንቀሳቀስ መሆኑን ሰምተናል ።

ኢትዮዽያ ቡና በዘንድሮ አመት በሊጉ በሚኖረው ውድድር ራሱን በተሻለ ለማጠናከር በማሰብ ከ10 በላይ ተጫዋቾችን ቢያስፈርምም የተጠበቀውን ያህል አገልግሎት አለመስጠታቸውን ተከትሎ  በመጀመርያው የውድድር አጋማሽ ላይ አጥቂዎቹን በረከት ይስሐቅ ፣ ማናዬ ፋንቱ እንዲሁም የመስመር ተከላካዮን አብዱሰላም ኑሩ ጋር በስምምነት መለያየታቸው  ይታወሳል።