ወልዋሎ ከራያ ቢራ ጋር የስፖንሰርሺፕ ውል ፈፅሟል

ባለፈው ሳምንት ከመቐለ ከተማ ጋር የሶስት ዓመት የስፖንሰርሺፕ ውል የተፈራረመው ራያ ቢራ  አሁን ደግሞ ከሌላው የትግራይ ክልል ክለብ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር ተመሳሳይ ውል ፈጽሟል።

ራያ ቢራ ከወልዋሎ ጋር የተፈራረመው የማልያ ስፖንሰርሺፕ ውል ለ3 ዓመታት የሚቆይ ሲሆን በነዚህ ጊዜያት 9 ሚልዮን ብር ወደ ክለቡ ካዝና ይገባል። ከዚህ በተጨማሪም ለደጋፊዎች ጥራቱን የጠበቀ ማልያ የሚያቀርብ ሲሆን በዓዲግራት እና አካባቢው ከሚሸጠው የቢራ ምርት ከአንድ ሳጥን ሁለት ብር ለክለቡ እንደሚሰጥ ታውቋል።

የቢራ አምራች ኩባንያው ከመቐለ ጋር 30 ሚልዮን ብር ገደማ ዋጋ ያለው የ3 ዓመታት ስምምነት መፈራረሙ የሚታወስ ነው።

በሀገራችን እግርኳስ የቢራ አምራቾች ተፅእኖ የቀጠለ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ዳሽን ቢራ የወልዲያ እና ፋሲል ከተማ፣ ሐበሻ ቢራ የኢትዮጵያ ቡና የማልያ ስፖንሰር ናቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አጋሮች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል።