አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ወደ አፄዎቹ ቤት አቅንተዋል 

ፋሲል ከተማ የ6 ወር ኮንትራቱን ከጨረሱት መሳይ ተፈሪ ጋር ከተለያየ ከቀናት በኋላ ሀዋሳ ከተማን የለቀቁት አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ለመቅጠር ከስምምነት መድረሱ ታውቋል።

በወጣት ተጨዋቾች ላይ በመስራት እና በኳስ ቁጥጥር ላይ መሰረት አድርጎ በጥሩ ፍሰት ለመጫወት የሚሞክር ቡድን ሲገነቡ የሚስተዋለው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቀጣይ ማረፊያቸው ጎንደር መሆኑ ተረጋግጧል። አሰልጣኙ ለሁለት አመት የሚቆይ ኮንትራት የሚፈርሙ ሲሆን ለዚህ ቆይታቸውም በወር የ60 ሺህ ብር ደሞዝ እና ተጨማሪ ጥቅማጥቅሞች እንደሚከፈላቸው ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 2003 ላይ የሊጉን ዋንጫ ማንሳታቸው የሚታወስ ነው። ከዚህ በተጨማሪም አዳማ ከተማ ፣ ሀዋሳ ከተማ እና በጎረቤት ሀገር የሱዳኑ አል አህሊ ሼንዲን ማሰልጠናቸው ይታወቃል። አሰልጣኝ  ውበቱ በፋሲል ከተማ በተሻለ የኳስ ፍሰት የሚጫወት ቡድን እንደሚሰሩና ደጋፊዎችን ለማስደሰት እንደሚጥሩ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

ክለቡ በነገው ዕለት ረፋድ ላይ በኢትዮጵያ ሆቴል ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ በይፋ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።