አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ እና አዳማ ከተማ ተለያዩ

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ ረዳታቸው በመሆን ሲሰሩ የቆዩት አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ በ2009 የውድድር ዘመን መጋቢት 20 በ17ኛ ሳምንት ይርጋለም ላይ በሲዳማ ቡና በሽንፈት ነበር ስራቸውን በጊዜያዊነት የጀመሩት ። በመቀጠል በ2010 ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት እንዲመሩ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ቆይተዋል።

ያለፉትን 18 ወራት ከአዳማ ከተማ ጋር ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ በተለይም በዘንድሮ ዓመት ለአዳዲስ ተጫዋቾች ቅድሚያ እድል በመስጠት እና በሜዳው የማይቀመስ ጠንካራ ቡድን በመገንባት ስኬታማ ጊዜ ቢያሳልፉም ከሜዳ ውጭ በሚያስመዘግቡት ደካማ ውጤት እና ቡድን በመምራት ብቃታቸው ላይ ጥያቄ ይነሳባቸው እንደነበረ ይታወቃል። የአዳማ ከተማ እግርኳስ ክለብ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ትላንት ባደረገው ስብሰባም ቡድኑ በቀጣይ ዓመት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀርብ በማሰብ የውል ዘመናቸው ከተጠናቀቀው አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ ጋር እንደማይቀጥል ከውሳኔ ደርሷል። በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥም ቀጣዩ አሰልጣኝ ከሀገር ውስጥ አልያም የውጭ ሀገር ሊቀጥር እንደሚችልም ለክለቡ ቅርበት ካላቸው አካላት ሰምተናል።

ባለፉት ሶስት ተከታታይ የውድድር ዓመታት በ3ኛነት ያጠናቀቀው አዳማ ከተማ ዘንድሮ በ44 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል።