ከፍተኛ ሊግ| ጅማ አባ ቡና ከመሪው ጋር በነጥብ ተስተካክሏል

በ25ኛው ሳምንት የከፍተኛ ሊግ ጨዋታ ጅማ አባ ቡና ሀምበሪቾ ዱራሜን በቴዎድሮስ ታደሰ የጭማሪ ደቂቃ ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ጅማ አባ ቡናዎች የተሻሻሉ ነበሩ። ነገር ግን እንደነበራቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የሀምበሪቾዎችን ጠንካራ የተከላካይ መስመር ለማለፍ ሲቸገሩ ተስተውለዋል። በ6ኛው ደቂቃ ሱራፌል ጌታቸው ከርቀት አክርሮ ወደ ግብ የመታው እንዲሁም ኬዳኔ አሰፋ በ9ኛው ደቂቃ ከተመሳሳይ ርቀት ያደረገው እና የግቡን ቋሚ ታኮ ወደ ውጭ የወጣው ሙከራ ተጠቃሽ ነበር። በተጨማሪም 19ኛው ደቂቃ ላይ ጀሚል በግራ ጠርዝ ሳጥን ውስጥ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ በቀላሉ ግብ ጠባቂው  ያዳነበት ኳስ በ22ኛው ደቂቃ ደግሞ ሱራፌል ጌታቸው ከጀሚል ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ውስጥ ገብተው ሃይደር ሸረፍ ያባከነው ኳስ ለቡድኑ የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ። ሀምበሪቾ ዱራሜዎች የመጀመሪያውን አጋማሽ ሙሉ በሙሉ በመከላከል ላይ መሰረት ባደረገ አጨዋወት ተጠምደው ያለምንም የግብ ሙከራ ጨርሰዋል።

ከእረፍት መልስ ሀምበሪቾዎች ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ ይዘው ቢገቡም ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ መከላከሉን ከመልሶ ማጥቃት ጋር በማቀናጀት ለግብ የቀረቡ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ከጅማ አባ ቡናዎች ተሽለው ታይተዋል። በ48ኛው ደቂቃ አገኘሁ ተፈራ በመልሶ ማጥቃት ከሶስት የቡድን አጋሮቹ ጋር ከአንድ  የአባቡና ተከላካይ ጋር ወደ ግብ ቢደርሱም የአባቡናው ግብ ጠባቂ በቀላሉ ያዳነበት ፣ 55ኛው ደቂቃ ጅላል ከማል በመልሶ ማጥቃት የግቡን ቋሚ የመለሰበት ፣ 57ኛው ደቂቃ ላይ ቴዲ ታደሰ ሞክሮ በድጋሚ የግቡ አግዳሚ ብረት የመለሰበት እንዲሁም በ68ኛው ደቂቃ ጫላ በንቲ የአባ ቡናው ግብ ጠባቂ ሙላቱ እንደ ምንም ያዳነበት ሙከራዎች ሀንበሪቾዎች አሸንፈው መውጣት የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። በ64ኛው ደቂቃ ፀጋሰው ደማሞ ጀሚል ያዕቆብ ላይ በሰራው ጥፍት በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። በአባ ቡና በኩል መረጋጋት ሲሳናቸው የታዩ ሲሆን የወሰዱትን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተጠቅመው ወደ ግብ የሚደረጓቸው ሙከራዎች ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ቢቀቱም የማታ ማታ ባለድል ሆነዋል። በዚህም በ95ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ጀሚል ያሻገረውን ኳስ ቴዎድሮስ ታደሰ በግንባሩ በመግጨት በሜዳቸው ነጥብ ከመጋራት የተረፉበትን ግብ በማስቆጠር ጨዋታው በአባ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የምድብ ሀ 26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች
ማክሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2010

04፡00 ፌደራል ፖሊስ ከ የካ ክ/ከተማ (ኦሜድላ ሜዳ)

04:00 ሱሉልታ ከተማ ከ አማራ ውሃ ስራ (ሱሉልታ)

04:00 ነቀምት ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን (ነቀምት)

04:00 ደሴ ከተማ ከ ኢኮስኮ (ደሴ)

04:00 ቡራዩ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ (ቡራዩ)

06:00 ወሎ ኮምቦልቻ ከ አክሱም ከተማ (ኦሜድላ ሜዳ)

06፡00 ባህርዳር ከተማ ከ ሽራ እንደስላሴ (አዳማ)

06:00 ለገጣፎ ለገዳዲ ከ አዲስ አበባ ከተማ (ለገጣፎ)