የአአ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽን የማሟያ ምርጫ ሊያደርግ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽን በተጓደሉ አባላት ምትክ ቀኑ ባልተገለፀ ጊዜ የፕሬዝደንት እና ስራ አስፈፃሚ ምርጫ ሊያደርግ መሆኑን ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

ለፕሬዝደንትነት ሁለት እና ለስራ አስፈፃሚነት አስራ አምስት እጩ ተወዳዳሪዎች የቀረቡ ሲሆን ለፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩት አቶ ተስፋዬ ካሳይ እና ኢንጂነር ኃይለየሱስ ፍስሃ ናቸው። አቶ ተስፋዬ ካህሳይ ከትግራይ ክልል ድጋፍ አግኝተው በግንቦት ወር ሰመራ ላይ በተካሄደው የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ ላይ ከአራቱ እጩ ፕሬዝደንት መካከል አንዱ የነበሩ ቢሆኑም በመጀመርያው የምርጫ ሂደት ላይ አነስተኛ ድምፅ አግኝተው ሁለተኛው ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ ራሳቸውን ከውድድር እንዳገለሉ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ የአአ ከተማን እግርኳስ ፌዴሬሽን በፕሬዝደንትነት ለመምራት እጩ ተወዳዳሪ በመሆን ቀርበዋል። ኢንጅነር ኃይለየሱስ ፍስሀም የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽንን በመወከል በአፋሩ የፌዴሬሽን ምርጫ ለስራ አስፈፃሚነት ከተወዳደሩት 22 እጩዎች አንዱ የነበሩ ቢሆንም በአቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በድምፅ ተበልጠው ሳያልፉ መቅረታቸው ይታወሳል።

ለስራ አስፈፃሚነት ከሚወዳደሩት 15 እጩ ተወዳዳሪዎች ውስጥ አንጋፋው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በአአ አሰልጣኞች ማኅበር በኩል የሚወዳደሩ ሲሆን በአፋሩ የምርጫ ጉባኤ ላይ ለስራ አስፈፃሚነት ሊወዳደሩ ቀርበው የነበረ ቢሆንም በምርጫው ሒደት ደስተኛ ባለመሆን ራሳቸውን ከእጩነት ማግለላቸው ይታወቃል።

የስራ አስፈፃሚ እጩ ተወዳዳሪዎች ስም ዝርዝር

አቶ አስራት ኃይሌ

አቶ ስንታየው እጅጉ

አቶ ድሪባ ክታን

ምትኩ መኩርያ (ኮሎኔል)

አቶ ደረጄ ደባስ

አቶ ዓለማየሁ አመርሳ

አይናለም ኃይሌ (ዶ/ር)

አቶ ወንድወሰን ተሰማ

አቶ ነጋሲ ሀለፎም

የማታወርቅ አበበ (ኢ/ር)

ወ/ሮ ሰርካለም ከበደ

አቶ ተስፋዬ ቶሳ

አቶ መስፍን መንግስቱ

አቶ የኔነህ በቀለ

አቶ ዳንኤል ፍቃዱ

የምርጫው አጣሪ ኮሚቴ ማንኛውም አካል በቀረበው ዝርዝር ላይ ቅሬታ ካለው እስከ ሐምሌ 19 10:00 ድረስ ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችል ተገልጿል።