ሦስት ተጫዋቾች ወደ ፋሲል አምርተዋል

ፋሲል ከነማ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ቀላቅሏል። ሐብታሙ ተከስተ፣ ሽመክት ጉግሳ እና በዛብህ መለዮ ወደ አጼዎቹ ቤት ያመሩ ተጫዋቾች ናቸው።

የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ሐብታሙ ተከስተ በ2008 ክረምት የፈረሰው ዳሽን ቢራን ለቆ መቐለ ከተማን የተቀላቀለ ሲሆን ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ እና በሊጉ 4 ሆኖ ሲያጠናቅቅ ወሳኝ ሚና ከተወጡ ተጫዋቾች አንዱ ነው። የ2 ዓመት ኮንትራት ከፋሲል ጋር የተፈራረመው ሐብታሙ የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የመጀመርያ ይፋዊ ፈራሚ ተጫዋች ሆኗል።


በዛብህ መለዮ በ2002 ወደ ሙገር ሲሚንቶ ወጣት ቡድን በማምራት የክለብ ህይወቱን ጀምሮ በሀዲያ ሆሳዕና የ3 ዓመታት ቆይታ በማድረግ በ2006 ወላይታ ድቻን ተቀላቅሎ በክለቡ የ5 ዓመት ቆይታው ድንቅ አቋሙን ማሳየት ችሏል። ተጫዋቹ ወደ ፋሲል ማምራቱን ተከትሎም የቡድኑን የፈጠራ ችግር ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላው ወደ ክለቡ ለማቅናት የተስማማው የመስመር አጥቂው ሽመክት ጉግሳ ነው። በ2004 ወላይታ ድቻን ለቆ ለሀዋሳ ከተማ ከፈረመ ወዲህ በሊጉ ወጥ አቋም ማሳየት የቻለ ሲሆን በ2006 ወደ ደደቢት አምርቶ እስከ ዘንድሮ የውድድር ዓመት መጨረሻ ድረስ ቆይታ አድርጓል።

ፋሲል በክረምቱ አዳዲስ ተጫዋቾች ከማስፈረም ጎን ለጎን የተጫዋቾቹን ውል በማደስ ላይ የሚገኝ ሲሆን ቴዎድሮስ ጌትነት፣ ያሬድ ባየህ፣ አምሳሉ ጥላሁን፣ ፍፁም ከበደ፣ ሰዒድ ሁሴን እና መጣባቸው ሙሉ ያራዘሙ ተጫዋቾች ናቸው።