ሶከር ሜዲካል፡ የአተነፋፈስ እከሎች በእግር ኳስ

በእግር ኳስ ተዘውትረው ከሚታዪ ችግሮች መካከል የትንፋሽ መቆራረጥ ወይንም ማጠር አንዱ ነው፡፡ እግርኳስ አድካሚ እና ብዙ ጉልበትን የሚጠይቅ ስፖርት ከመሆኑ አንጻር እንደዚህ አይነቱ ጉዳት በብዛት ይታያል፡፡ በዛሬው የሶከር ሜዲካል አምዳችን የዚህን ችግር መንስኤዎች፣ ምልክቶች እና መደረግ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች ከመጀመሪያ ደረጃ እርዳታዎች ጋር እንመለከታለን፡፡

የአተነፋፈስ ችግሮች በሁለት ዋና ምክንያቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ አንደኛው መንገድ ተጫዋቹ ቀድሞውኑ የታወቀ በሽታ ካለበት በጨዋታ መሃል የማገርሸት እድሉ እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ እንደ አስም የመሳሰሉ በሽታዎች በቂውን ክትትል እና ህክምና ካላገኙ ለከፋ የጤና መቃወስ ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡

ሁለተኛው ችግር በጨዋታ መሃል በግጭት የሚያጋጥም ነው፡፡ የአየር ቱቦ መዘጋት (airway obstruction) አልያም መታፈን እና አየር ማጠር ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በቅርቡ እንኳን በከፍተኛ ሊግ በተደረገ ጫወታ የባህር ዳር ከተማው ሚኪያስ ግርማ ከግብ መቆጠር መልስ በመደራረብ ደስታ በሚገለጽበት ወቅት ታፍኖ በዛው ቅፅበት ራሱን ስቶ በመውደቁ ለህክምና ወደ ሆስፒታል የተላከበት አጋጣሚ የሚታወስ ነው።

በተለምዶ አንድ ተጫዋች በሜዳ ላይ ራሱን ስቶ የአየር ቱቦ በሚዘጋበት ጊዜ “ምላሱን ውጦ“ የሚል አገላለጽ አለ፡፡ ይህ ትክክለኛ ያልሆነ አገላለፅ ነው፤ ምላስ ተውጦ ሳይሆን በመታጠፉ እና ወደ እንጥላችን የሚወስደውን የአየር መንገድ በመዝጋቱ የሚፈጠር ነው፡፡ ይህ ጉዳት ተዘውትሮ ከሚታዩ አጣዳፊ ህክምና ከሚያስፈልጋቸው ችግሮች መካከል አንዱ እና ዋንኛው ነው፡፡

እንድ ሰው የአተነፋፈስ እከል ሲያጋጥመው የተለያዮ ምልክቶችን የሚያሳይ ሲሆን እነዚህም በሃይል መተንፈስ ፤ የትንፋሽ ማጠር ፤ የአፍንጫ መርገብገብ ፤ የቆዳ ቀለም የመጥቆር ነገር ማሳየት፤ ከትንፋሽ ጋር ተጨምረው የሚሰሙ እንደማፋጨት ያሉ ድምጾች፤ ራስን መሳት እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

እንደዚህ አይነት ከአተነፋፈስ ጋር የተያያዙ እከሎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ህክምና የሚሰጠው እዛው ሜዳ ላይ ነው፡፡ በመጀመሪያ እርዳታ የተዘጋውን የአተነፋፈስ መንገድ ለማስከፈት ተጫዋቹ በጀርባው ከተደረገ ቀጥሎ ጭንቅላቱ ወደ ኋላ ገፋ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ከዚህ በመቀጠልም የታጠፈውን ምላስ ጣትን አፍ ውስጥ በመጨመር ለመመለስ ሙከራ የሚደረግ ሲሆን ከአፍ ወደ አፍ አየርን በማስተላለፍ እንደዚሁም ደረት ላይ በመጫን የአተነፋፈስ ስርአቱን CPR (Cardio-Respiratory Resuscitation)በተሰኘው የመጀመሪያ እርዳታ መንገድ ለመመለስ ጥረት የሚደረግ ይሆናል፡፡ በስፍራው የህክምና ባለሞያዎች ከድንገተኛ ህክምና መስጫ ቁሳቁሶችን ይዘው ከተገኙ ደግሞ የተለያየ አይነት ያላቸው የመተንፈሻ ቱቦዎችን በመጠቀም የአየር መተላለፊያ ቱቦዎች እንዳይዘጉ ያደርጋሉ። አተነፋፈሱ መመለሱ ከታወቀ ቀጥሎ ነው ሌሎች ምርመራዎች እና ህክምናዎች የሚሰጡት፡፡

በቂ እውቀት ያካበቱ ባለሞያዎች በብዛት በሌሉበት የኢትዮጵያ እግርኳስ እንደዚህ ያለው ህይወት እስከማጣት የሚያደርስ ችግር እንዳይፈጠር ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ እንደ ስብራት እና ውልቃት እንዳሉ ጉዳቶች ጊዜ የሚሰጥ ስላልሆነ እና ችግሩ ባጋጠመበት ቅፅበት መፍትሄ የሚጠይቅ በመሆኑ አፋጣኝ ህክምና የሚደረግበትን መንገድም ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በመጫወቻ ሜዳዎች ላይ የአንቡላንስ እና የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎች ማስፈለጋቸው ዋንኛው ምክንያትም እንደዚህ ላሉ ችግሮች መፍትሄን ለማበጀት ነው፡፡ ከጨዋታ ውጪም በልምምድ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ መሰል አደጋዎችን ለመከላከል በልምምድ ሜዳዎች ላይ የህክምና ባለሞያዎች እና በቂ የህክምና ቁሳቁሶች እንዲኖሩ ማድረግም ከክለቦች ይጠበቃል።

ለተጫዋች እና ለአሰልጣኞች ዝውውር መጠኑ የበዛ የዝውውር ገንዘብ እያወጡ የሚገኙት ክለቦቻችን የህክምና መዋቅራቸውን በማዘመን ብዙ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሱባቸውን ተጫዋቾች ደህንነት ለማረጋገጥ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡

error: