ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ኢስማይሊ አምርቷል

የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ጎል አስቆጣሪው ኦኪኪ አፎላቢ የግብፁ ኢስማይሊን መቀላቀሉን ክለቡ ይፋ ድርጓል።

ናይጄርያዊው አጥቂ በዓመቱ መጀመርያ በተቀላቀለበት በጅማ አባጅፋር ውጤታማ ጊዜ በማሳለፍ ክለቡን ለሊግ ቻምፒዮንነት ሲመራ ሁለት ሐት-ትሪኮችን ጨምሮ 23 ጎሎችን በውድድር ዓመቱ በማስቆጠር በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ማጠናቀቅ ችሏል።

ኦኪኪኦላ አፎላቢ የተጫዋችነት ህይወቱን በሀገሩ ክለብ ሰንሻይን ስታርስ ጀምሮ ወደ አርጀንቲናው ታሌሬስ ዲ ኮርዶባ አምርቶ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በጅማ አሳልፏል። አሁን ደግሞ የግብፅ ፕሪምየር ሊግን በሁለተኝነት አጠናቆ በቀጣዩ ዓመት በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሚካፈለው ኢስማይሊን ተቀላቅሏል።

ከሊጉ ቻምፒዮን ጅማ አባጅፋር እስካሁን 3 ተጫዋቾች መልቀቃቸው የተረጋገጠ ሲሆን ኮንትራታቸው የተጠናቀቁ ተጫዋችችን ውልም ማራዘም አልቻለም። የአሰልጣኙ ቆይታ እርግጥ አለመሆንም ለክለቡ ተጨማሪ የክረምት የቤት ስራ ሆኗል።