ባህርዳር ከተማ አቀባበል ተደርጎለታል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር በምድብ ሀ 3 ጨዋታ እየቀረው በቀጣይ አመት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ለግ መሳተፉን ያረጋገጠው ባህርዳር ከተማ ትላንት ምሽት ወደ ከተማው ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። በብሉ ናይል ሆቴል እና ስፓም የገቢ ማሰባሰቢያ (ቴሌቶን) መርመየሐ ግብር ተከናውኗል።

ትላንት በመድን ሜዳ በተደረገው የ28ኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድንን በሙሉቀን ታሪኩ እና በግርማ ዲሳሳ ሁለት ጎል ጨዋታውን ያሸነፈው ባህር ዳር ከተማ ትላንት ምሽቱን ወደ ከተማው ሲገባ በባህርዳር የአየር ማረፊያ እና በባህርዳር ከተማ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። ሶስት ጨዋታዎች እየቀሩት ከወዲሁ ማለፉን ያረጋገጠው የአሰልጣኝ ጳውሎስ ስብስብ በ61 ነጥብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጣይ አመት በሀገሪቱ ዋናው ሊግ ተሳታፊ የሚሆን ሲሆን ቡድኑ በቀጣይ ጠንካራ እና ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ የፋይናንስ አቅሙን ለማሳደግ የመጀመሪያ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን እና የድጋፍ ሽልማት ትላንት ምሽት በብሉ ናይል ሆቴል እና ስፓ ተደርጎለታል።

የክልሉ መንግስት 5 ሚሊዮን ብር እና 1 ዘመናዊ አውቶብስ ጨምሮ የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም በከተማው የሚገኙ የመንግስት እና የግል መስሪያ ቤቶች ለቡድኑ የፋይናንስ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በአጠቃላይ በትላንት ምሽቱ ፕሮግራም ከዘጠኝ ሚሊዮን ስምንት ምቶ ሰባ ሺ(9,870,000) ብር በላይ መገኘቱ ተገልጿል። ከዚህ ቀደም የተለያዩ የግል ድርጅቶች ቃል የገቡትን ሽልማት ሲያበረክቱ ደግሞ ከዚህ የተሻለ ገቢ እንደሚገኝ ይጠበቃል።

ከዚህ ቀደም የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ክለቡ  ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት የሚያደርገውን ጉዞ በስኬት ካጠናቀቀ ለክለቡ ተጫዋቾች እና አመራሮች የማበረታቻ ሽልማት እሰጣለው ብሎ ቃል መግባቱ የሚታወስ ሲሆን ለክለቡ 25 ተጨዋቾች ለእያንዳንዳቸው 100 ካ.ሜ ቦታ እና አንድ መቶ ሺ ብር (100,000) እንዲሁም ለዋናው አሰልጣኝ 100 ካ.ሜ ቦታ እና ሁለት መቶ ሺ ብር(200,000) በሽልማት መልክ የሚሰጠው ማበረታቻ በቅርብ ጊዜ እንደሚፈፀም ተነግሯል።