መቐለ ከተማ 5ኛ ተጫዋቹን አስፈርሟል

ገብረመድህን ኃይሌን አሰልጣኝ አድርጎ የመረጠው መቐለ ከተማ በዝውውር መስኮቱ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ያሬድ ሀስንንም የክለቡ 5ኛ አዲስ ፈራሚ አድርጎ ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አማካይ ከወልዲያ ያለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት ቆይታ በኋላ በመልቀቅ የሰሜን ኢትዮጵያውን ክለብ በአንድ ዓመት ውል ተቀላቅሏል። የግራ እግር ተጫዋቹ ያሬድ ከአማካይነት በተጨማሪ በመስመር ተከላካይነት መጫወት የሚችል ተጫዋች ነው።

መቐለ እስካሁን አምስት ተጫዋቾችን ሲያስፈርም ከክለቡ ጋር የማይቀጥሉ ተጫዋቾችንም እየለየ ይገኛል። ሐብታሙ ተከስተ እና ጋቶች ፓኖም ወደ ሌሎች ክለቦች ሲያመሩ በውድድር ዓመቱ አጋማሽ ክለቡን ተቀላቅለው ብዙም ግልጋሎት ያልሰጡት ካርሎስ ዳምጠው፣ እያሱ ተስፋዬ እና ቶክ ጀምስ ከክለቡ ጋር የማይቀጥሉ ተጨዋቾች መሆናቸው ተገልጿል።