“ጠንካራ ጎናችን ስብስባችን ነው” የባህር ዳር ከተማ አምበል ደረጄ መንግስቱ 

በሁለት ምድቦች ተከፍሎ እየተደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር በቀጣይ አመት ወደ ዋናው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚያድገውን ክለብ የሚወስን ሲሆን በምድብ ሀ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ ከሜዳው ውጪ ኢትዮጵያ መድንን ገጥሞ በማሸነፍ ቀሪ ሶስት ጨዋታዎች እየቀሩት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል። በ1973 ዓም እንደተመሰረተ የሚነገርለት ባህር ዳር ከተማ ለአመታት ሲመኘው እና ሲጠብቀው የነበረውን ስኬት ዘንድሮ ያሳካ ሲሆን በከፍተኛ ሊጉ ከሚወዳደሩ እና በሁለቱም ምድብ ከሚገኙ ክለቦች ቀዳሚው አዲስ አዳጊ ክለብ ሆኗል። በ27 ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት ብቻ ያስተናገደው ባህር ዳር ከተማ በጠንካራነቱ የሚታወቅ ሲሆን የዚህ ቡድን ዋና አምበል የሆነው እና ቡድኑ በሜዳውም ሆነ  ከሜዳውም ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ድንቅ ብቃቱን በማሳየት ሲያገለግል የነበረው ደረጄ መንግስቱ ስለ ቡድኑ ስኬት እና ስላሳለፈው አመት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ዓመቱ እንዴት ነበር ? በግልም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገን ክለብ በአምበልነት መርተሀል እንደ ቡድንም ጠንካራ ስብስብ ባለው ክለብ ውስጥ ተሳትፈህ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድጋችኋል እና አመቱን እንዴት ትገልፀዋለህ?

ዓመቱ እጅግ በጣም አሪፍ ነበር። በግሌም ጥሩ የውድድር አመት አሳልፌያለው ፤ ዋና አላማዬ ደግሞ ክለቤን ወደ ሊጉ እንዲገባ ማገዝ  ስለነበረ እና ልፋቴ ፍሬ በማፍራቱ የአመቱን አጨራረስ አሳምሮልኛል። እንደ ቡድን አመቱን በጥሩ ሁኔታ አልጀመርንም ነበር። አቻዎችን አብዝተን ድንጋጤ ውስጥ ገብተን ነበረ። የተወሰኑ ደጋፊዎችም ከጉጉት የተነሳ ውጤት ሲርቀን የተወሰነ ጫና አሳድረውብን ተደናግጠን ነበር። ነገር ግን ቶሎ ማገገም እንዳለብን  እና ዋና አላማችንን ማሳካት እንዳለብን በማሰብ ጠንከር ያሉ ስራዎችን በመስራት አገግመን ለዚህ ድል በቅተናል።

እንደሚታወቀው በ27 ጨዋታ ሁለት ሽንፈት ብቻ ነው ያስተናገዳችሁት እና ጥንካሬያችሁ ምን ነበር ?

ጠንካራ ጎናችን ስብስባችን ነው። በቡድናችን ውስጥ ብዙ ጠንካራ እና ታጋይ ልጆች አሉ ይህ ደግሞ ለስኬታችን ዋነኛ ሚስጥራችን ነው። ቡድናችን ውስጥ ተጠባባቂ የሚሆኑትም ሆነ ከተጠባባቂ ውጪ የሚሆኑት ልጆች እጅግ ጠንካራ ናቸው። ሌላ ቡድን ውስጥ  ቢሆኑ ያለ ጥርጥር ቋሚ ሊሆኑ የሚችሉ ተጨዋቾች ናቸው። ነገር ግን 11 ተጫዋች ብቻ ነው እና ወደ ሜዳ የሚገባው ልዩነቶች መጡ እንጂ በጣም ጠንካራ ስብስብ ነበረን። በከፍተኛ ሊግም ሆነ በፕሪሚየር ሊግ ያሉ አንዳንድ ክለቦች ላይ የሚታዩ የመናናቅ እና ያለመከባበር ነገሮች እኛ ቡድን ላይ ፈፅሞ የሉም። በቡድናችን የተለያየ የብቃት ደረጃ ላይ ያለ ተጨዋች እንኳን ማንንም የቡድኑን ተጨዋች አይንቅም ፤ በተለየ አይን አያይም። ሁላችንም በፍቅር በአንድነት እና በመከባበር ነው አመቱን ያሳለፍነው።

ውድድሩ እንዴት ነበር ? በፈታኝነቱ እና በፉክክሩ የሚታወቀው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ምን ምን ፈታኝ ነገሮች ነበሩበት ?

ውድድሩ አድካሚ እና አሰልቺ ነው። ከሚጀመርበት ቀን አንስቶ እንከን የማይጠፋው ውድድር እንደመሆኑ ለተጨዋቾች ፈታኝ ያደርገዋል ፤ በተለይም በሜዳ ችግሮች። እኛ እንኳን እንደሚታወቀው ባለ ግዙፍ እና አመቺ ስታድየም ባለቤት ነን ፤ በሜዳችን በምናደርጋቸው ጨዋታዎች  አንቸገርም። ነገር ግን ከሜዳ ውጪ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች በጣም ነው የምንቸገረው። ለጨዋታ ብቁ ባልሆኑ አጥር የለሽ ሜዳዎች እና ተጨዋችን ጉዳት ላይ በሚጥሉ ሜዳዎች ላይ እንድንጫወት እንገደዳለን። ይህ ደግሞ በጣም ፈታኝ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የፕሮግራም አወጣጡ በጣም ልክ ያልሆነ ነው። የጨዋታ መደራረቦች ሲያጋጥሙን ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን ባለቀ ሰዓትም ጨዋታ እንዳለን እያወቅን የሚለወጥበት ጊዜም አለ። ይህ ለተጫዋች በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው። ለቀጥይ አመታት ግን ፌደሬሽኑ ስራዎችን ሰርቶ እንደዚህ አይነት ችግሮች እንዳይፈጠሩ ማድረግ አለበት።

ከቡድኑ የአሰልጣኝ ክፍል በተጨማሪ የክለቡ አመራሮችስ ድጋፍ ያደርጉላችሁ ነበር?

የክለቡ አመራሮች በጣም ይደግፉን ነበር። ከመጀመሪያው እለት አንስቶ የሚቸግሩንን ነገሮች ከማስተካከል በተጨማሪ የተለያዩ የማበረቻቻ ድጋፎችን እያደረጉልን ከጎናችን ነበሩ። ወደ ፕሪምየር ሊግ መግባት አሁን ወይም የውድድሩ አጋመሽ ላይ የታቀደ ዕቅድ  አይደለም። ከአምና ጀምሮ አመራሮቹ እንደ እቅድ ይዘውት ስራዎችን ሲሰሩ የነበሩበት ሁኔታ ነው እና የኛ ልፋት ብቻ ሳይሆን የሁሉም አመራሮች የልፋት ውጤት ነው እዚህ ያደረሰን።

ባህርዳር ከተማ ከዚህም አመት በፊት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመግባት ጫፍ እየደረሰ በአጨራረስ ችግር ሳይሳካለት አመታትን ጠብቋል ዘንድሮ ምን ምን ለውጦች ስለመጡ ነው የተሳካላችሁ?

ባህርዳር ባለ ብዙ እና ውብ ደጋፊዎች ባለቤት ነው። በከፍተኛ ሊጉ ላይ መወዳደር በጣም ያንስበታል። ይህ ደግሞ እኛ ተቆጭተን እንድንጫወት እና ከፍተኛ ጥረት እንድናደርግ አድርጎናል። በመሆኑም አላማችንን ዘንድሮ እንድናሳካ አድርጎናል። ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ በጀት በጅቶ አዳዲስ ተጨዋቾችን ከማስፈረም እና ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን አሰልጣኞች ከማምጣት ጀምሮ ብዙ ስራዎች ዘንድሮ መስራታችን የፈለግነውን እንድናገኝ አድርጎናል።

ስለ ደጋፊዎቻችሁስ ምን ትላለህ?

ስለ ደጋፈከዎቻችን ምን ማለት እንዳለብኝ አላውቅም። በጣም የሚገርም ደጋፊ ነው ያለን በየቦታው ስንሄድ ከጎናችን ሆኖ እያበረታታ አይዟችሁ እያለ ሲደግፈን ነበር። ነገር ግን ከላይ እንደጠቀስኩት መጀመሪያ አካባቢ የነበረው ነገር ትንሽ ደስ አይልም ነበር። ቢሆንም እኛም እነሱን ለማስደሰት ስንጥር አነሱም ከኛ ጎን ሲሆኑ ለዚህ ስኬት በቅተናል። በአጠቃላይ ግን ስለደጋፊዎቻችን ቃላት የለኝም በምን እንደምገልፃቸው።

ቡድናችሁ በቀጣይ በሊጉ ላይ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ምን ምን ስራዎች መሰራት አሉበት ብለህ ታምናለህ ?

በቀጣይ አመት በሊጉ ላይ ተፎካካሪ ለመሆን ሁሉም ቡድናችን አካባቢ ያሉ ሰዎች ስራዎችን ከወዲሁ መጀመር አለባቸው። እንደ ቡድን ገና አልተነጋገርንም። ነገር ግን በግሌ ቡድኑ በቀጣይ አመት በሊጉ ለመቆየት እና  ዕድሜውን ለማራዘም ይወዳደራል የሚል እምነት የለኝም። ዘንድሮ በሊጉ ያየናቸው ጅማ አባጅፋር እና መቐሌ ከተማ ለኛ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። ከከፍተኛ ሊግ ባደገበት አመት አንድ ቡድን ተፎካክሮ ዋንጫ እንደሚበላ እና ከነባር ክለቦች በላይ እንደሚሆን ዘንድሮ አይተናል። ይህ ደግሞ በይቻላል መንፈስ የተሻለ ነገር እንድናመጣ ያደርገናል። በግሌ ቡድኑ ዘንድሮ የነበሩበትን ክፍተቶች ለመድፈን ቶሎ አዳዲስ ተጨዋቾችን ከማስመጣት ጀምሮ ሌሎች  ስራዎችንም መስራት አለበት ብዬ አምናለው። እንደሚታወቀው የኛ ውድድር ሊያልቅ ሲል ነው የፕሪሚየር ሊጉ ቡድኖች ለቀጣይ አመት የዝግጅት ጊዜያቸውን የሚጀምሩት። ስለዚህ ሶስት ጨዋታ እየቀረን ወደ ሊጉ ማደጋችን ከነሱ አኩል ባንሆንም በገበያው ላይ ያሉ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾችን ተፎካክረን እንድናገኝ ያደርገናል ስለዚህ ስራዎች ቶሎ ቢሰሩ ባይ ነኝ።

በቀጥይ ያንተስ ቆይታ ? እንደሚታወቀው ኮንትራትህ አልቋል ከባህር ዳር ከተማ ጋር ትቀጥላለህ?

አዎ ኮንትራቴ አልቋል። ግን በቀጣይ ምን እንደሚመጣ ስለማላውቅ ይሄ ነው ብዬ መናገር ይከብደኛል። ነገር ግን ቀጣይ ዓመትም ለባህርዳር  መጫወት እፈልጋለሁ።