መከላከያ ሦስት ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል

መከላከያ የሦስት ተጫዋቾችን ፊርማ በዛሬው እለት አጠናቋል። ፍቃዱ ዓለሙ፣ ዳዊት ማሞ እና ዓለምነህ ግርማ የጦሩ ንብረት የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው።

ዳዊት ማሞ እና ፍቃዱ ዓለሙ ከቀድሞ አሰልጣኛቸው ሥዩም ከበደ ጋር ተገናኝተዋል። የአጥቂ አማካዩ ዳዊት እና አጥቂው ፍቃዱ አአ ከተማ ባለፈው ዓመት ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያልፍ ከረዱት ተጫዋቾች መካከል የነበሩ ሲሆን ክለቡ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ ሲወርድም አብረው ቆይታ አድርገዋል። አሁን ደግሞ ከአንድ የውድድር ዓመት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚመልሳቸውን ዝውውር በማድረግ የ2 ዓመት ውል ፈፅመዋል።

ሌላው ክለቡን የተቀላቀለው ዓለምነህ ግርማ ነው። የቀድሞው የአዳማ ከተማ፣ ንግድ ባንክ፣ ኤሌክትሪክ እና መቐለ ከተማ ተከላካይ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ መቐለን ከለቀቀ በኋላ ስሙ ከመከላከያ ጋር ቢያያዝም ወደ ወልዋሎ ማምራቱ የሚታወስ ነው። አሁን ደግሞ ወደ ጦሩ በ2 ዓመት ኮንትራት አምርቷል። በቴዎድሮስ በቀለ ተደጋጋሚ ጉዳት ሁነኛ የግራ ተከላካይ ተጫዋችን ለማግኘት የተቸገረው መከላከያ ቦታውን በዓለምነህ እንደሚሸፍን ይጠበቃል።