መከላከያ ሶስት ተጫዋቾች አስፈርሟል

መከላከያ በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳታፊ መሆኑን በመቀጠል ዛሬ የሶስት ተጫዋቾችን ፊርማ አጠናቋል።

ፍሬው ሰለሞን ወደ ቀድሞ ክለቡ ከሁለት ዓመታት በኋላ ተመልሷል። በ2005 ሙገር ሲሚንቶን ለቆ ጦሩን ከተቀላለ በኋላ በክለቡ ምርጥ ዓመታትን ያሳለፈው ፍሬው በ2009 ወደ ሀዋሳ አምርቶ በተለይ በመጀመርያ ዓመቱ ድንቅ ጊዜን አሳልፏል። የሀዋሳ ውሉን በመጨረሱም ወደ ቀድሞ ክለቡ በሁለት ዓመት ኮንትራት መመለስ ችሏል።

አበበ ጥላሁን ሌላው የመከላከያ አዲስ ፈራሚ ነው። በሊጉ ከሚገኙ ወጥ አቋም ከሚያሳዩ ተከላካዮች አንዱ የሆነው አበበ በ2009 አርባምንጭን ለቆ ወደ ሲዳማ ቡና በማምራት ሁለት ዓመታትን በክለቡ ቆይታ አድርጓል። አሁን ደግሞ በሁለት ዓመት ኮንትራት የጦሩ ንብረት ሆኗል። የአበበ መምጣት ባለፈው ዓመት በጉዳት የተቸገረውን የተከላካይ መስመር ያጠናክራል ተብሎለታል።

ብሩክ ቃልቦሬ ሶስተኛው አዲስ ፈራሚ ነው። የተከላካይ አማካዩ በወድድድር ዓመቱ መጀመርያ አዳማን ለቆ ወደ ወልዲያ ካመራ በኋላ ቡድኑ ከፋሲል ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ ያልተገባ ባህርይ አሳይቷል በሚል የአንድ ዓመት እገዳ የተላለፈበት ብሩክ የቅጣት ጊዜውን ባይጨርስም በይፋ በዛሬው እለት የመከላከያ ንብረት ሆኗል። የቀድሞው የመተሐራ ስኳር፣ ወላይታ ድቻ፣ አዳማ እና ወልዲያ ተጫዋች በጦሩ ቤት ለሁለት ዓመት የሚቆይ ይሆናል።