ጅማ አባ ጅፋር ፊቱን ወደ አሰልጣኝ ዘማርያም አዙሯል

የፕሪምየር ሊጉ ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር ከአሰልጣኙ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር ከተለያየ በኋላ አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌን ለመቅጠር ከስምምነት ቢደርስም ኮንትራት ሳይፈራረሙ መቅረታቸው ይታወሳል።

ባደገበት አመት የሊጉ ሻምፒዮን በመሆን አዲስ ታሪክ መፃፍ የቻለው ጅማ አባ ጅፋር በድሉ ማግስት የዝውውር መስኮቱ ከተከፈተ በኋላ ግን አሰልጣኙን ጨምሮ ቁልፍ ተጨዋቾቹን ለማጣት ተገዷል። ቀጣዩን የውድድር አመትም በአዲስ አሰልጣኝ እየተመራ አዲስ ቡድን የመገንባት እጣ ደርሶታል። ዛሬ በተሰማው ዜና ግን የአፍሪካ ሽምፒዮንስ ሊግ ላይ የመሳተፍም ፈተና የሚጠብቀው ክለቡ ቡድኑን እንደ አዲስ አዋቅሮ ለቀጣዩ የሊግ ውድድር አመት ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን አዲስ አሰልጣኝ ሾሟል። ይህን ሀላፊነት በመሸከም ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ለመያዝ የተስማማው ደግሞ አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ነው።

አሰልጣኝ ዘማርያም ፋሲል ከተማን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማሳደግ የቻለ አሰልጣኝ ሲሆን በፍጥነት በተጋጣሚ ሜዳ ላይ የሚደርስ ቡድን በመገንባት ክለቡ በመጀመሪያው የሊጉ ቆይታው ጥሩ የውድድር አመት እንዲሳልፍ እና መልካም ውጤት ይዞ እንዲያጠናቅቅ አስችሏል። በዘንድሮው የውድድር አመት ደግሞ ወልዲያን በመረከብ አመቱን የጀመረ ቢሆንም ከአፄዎቹ ጋር ያሳለፈውን ጥሩ ጊዜ መድገም ሳይችል ቡድኑ በውጤት እየተንሸራተተ ባለበት ሰዐት ላይ ደግሞ ከቀድሞው ክለቡ ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይ በተፈጠረ ረብሻ ምክንያት ለአንድ ዓመት ቅጣት ተዳርጎ እንደቆየ ይታወሳል። አሰልጣኙም ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት በእገዳው ዙርያ እስካሁን ይግባኝ አለመጠየቃቸውን ገልፀው ጉዳያቸውን በጅማ በሚኖራቸው ቆይታ እንደሚከታተሉ ገልፀዋል።

ጅማ ለሊጉ ቻምፒዮንነት ወሳኝ ሚና የተጫወቱ ተጫዋቸችን ቢያጣም እሰካሁን ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን በእጁ አስገብቶ የ7 ተጫዋቾች ውል አድሷል።