ከፍተኛ ሊግ | በምድብ ለ ፉክክሩ ቀጥሏል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 28ኛ ሳምንት እና የምድብ ለ 26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነዋል። በምድብ ለ መሪዎቹ በማሸነፋቸው ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ የሚደረገው ፉክክር ለቀጣዩ ሳምንት ተሸጋግሯል። 

ሀዋሳ ላይ የምድብ ለ መሪው ደቡብ ፖሊስ ቤንች ማጂ ቡናን ያስተናገደበት ጨዋታ በባለሜዳው አሸናፊነት ተጠናቋል። ጨዋታው ሙሉ ለሙሉ የባለሜዳው የበላይነት የታየበት ነበር። የመጀመሪያዎቹን 15 ደቂቃዎች ተጭነው ሲጫወቱ በነበሩት ፖሊሶች በኩል ገና በ6ኛው ደቂቃ ላይ አበባየሁ ዮሀንስ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ከ30 ሜትር ርቀት መቐለ ከተማን ለቆ ደቡብ ፖሊስን የተቀላቀለው ዱላ ሙላቱ አክርሮ በመምታት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ከግቧ በኃላ ፖሊሶች እጅግ በርካታ የግብ አጋጣሚን በህሩክ ኤልያስ ሚካኤል ለማ እና በተለይ በአማካዩ አበባየሁ ዮሀንስ አማካይነት ቢፈጥሩም መጠቀም ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተገባዷል።

ከእረፍት መልስ በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ተወስዶባቸው የነበሩት ቤንች ማጂ ቡናዎች በመጠኑም ቢሆን ተሻሽለው ሲታዩ ደቡብ ፖሊሶችም ብልጫቸውን ቢያስቀጥሉም ግብ ለማስቆጠር ግን ተቸግረው ታይተዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ የቤንች ማጂው የመስመር ተጫዋች ሀቲፍ ሙሀዲን ከግብ ጠባቂው ሀብቴ ከድር ጋር ተገናኝቶ ሀብቴ ቢመልስበትም 56ኛው ደቂቃ ላይ የቀድሞው የወልድያ አጥቂ ጋናዊው ኤሪክ ኮልማን የደቡብ ፖሊስ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ግሩም ግብ አስቆጥሮ ፖሊስን ስጋት ውስጥ በመክተት ማጂዎችን አነቃቅቷቸዋል፡፡ 76ኛው ደቂቃ ላይ በብሩክ ኤልያስ ላይ የቤንች ማጂ ተጫዋቾች በሰሩት ጥፋት በግራ የግቡ አቅጣጫ የተሰጠውን የቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው አጥቂው በኃይሉ ወገኔ አስቆጥሮ ደቡብ ፖሊስ ሶስት ነጥብ እንዲያገኝ እና መሪነቱን በማስቀጠል ከጅማ አባቡና እና ሀላባ ከተማ በአንድ ነጥብ በልጦ እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡

ወደ ቡታጅራ አምርቶ ቡታጅራ ከተማን የገጠመው   ከተማ 1-0 አሸንፏል። ሀላባን ድል ያስጨበጠች ብቸኛ ጎል ያስቆጠረው አቦነህ ገነቱ ነው። ሀላባ በድሉ ከደቡብ ፖሊስ ጋር ያለውን ርቀት በአንድ ነጥብ አስጠብቋል። ወደ መቂ ያቀናው ጅማ አባ ቡና በሱራፌል ጌታቸው እና ዳዊት ተፈራ ጎሎች መቂ ከተማን 2-0 አሸንፏል። በውጤቱም ከሀላባ ጋር በተመሳሳይ ነጥብ ከደቡብ ፖሊስ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ መከተሉን ቀጥሏል።

በሌሎች ጨዋታዎች ዲላ ናሽናል ሴሜንትን ከመመራት ተነስቶ በኤልያስ እንድሪያስ፣ ኩሴ መጠራ እና ኄኖክ አየለ ጎሎች 3-1 በማሸነፍ መሪዎቹን ሲከተል ሀዲያ ሆሳዕና ከረጅም ጊዜ በለላ ወደ ግብ አስቆጣሪነት በተመለሰው ኢብሳ በፍቃዱ ጎል ወልቂጤ ከተማን 1-0 አሸንፏል።  ሻሸመኔ ከተማ ከመውረድ ለመትረፍ በሚያደርገው ትግል ወሳኝ የ1-0 ድል ድሬዳዋ ፖሊስ ላይ አስመዝግቧል። ስልጤ ወራቤ በገብረመስቀል ዱባለ ጎል ሀምበሪቾን ከሜዳው ውጪ ሲያሸንፍ ነጌሌ ከተማ ካፋ ቡናን 2-1 አሸንፏል።

የደረጃ ሰንጠረዥ

በምድብ ሀ 28ኛ ሳምንት ዛሬ 3 ጨዋታዎች ተከናውነዋል። ሱሉልታ ከተማ በኢሳይያስ ዓለምእሸት ጎል ኢትዮጵያ መድንን 1-0 ሲያሸንፍ ነቀምት ከተማ ሰበታ ከተማን 2-0 ረቷል። ወደ ቡራዩ ያቀናው አክሱም ከተማ በቢንያም ጌታቸው የ89ኛ ደቂቃ ጎል 1-0 ማሸነፍ ችሏል።

የነገ መርሐ ግብር 

ባህርዳር ከተማ 4:00 ኢኮስኮ

ፌደራል ፖሊስ 4:00 አማራ ውሃ ስራ

የካ 6:00 ሽረ እንዳሥላሴ

አአ ከተማ 6:00 ደሴ ከተማ

ወሎ ኮምቦልቻ 4፡00 ለገጣፎ ለገዳዲ

የደረጃ ሰንጠረዥ