ወልዋሎ ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾች አስፈረመ

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በዝውውር መስኮቱ 7ኛ እና 8ኛ ዝውውሩን አጠናቋል። ደስታ ደሙ እና ሮቤል አስራት ቢጫ ለባሾቹን የተቀላቀሉ ተጫዋቾቹን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ደስታ ደሙ ከሙገር ሲሚንቶ በመልቀቅ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በደደቢት የቆየ ሲሆን ከፍተኛ መሻሻል በማሳየት መደበኛ ተሰላፊ መሆን ችሏል። በቀኝ እና መሀል ተከላካይነት መጫወት የሚችለው ደስታ ወልዋሎን የአንድ ዓመት ኮንትራት የተቀላቀለ ሲሆን ቡድኑ በክረምቱ የተከላካይ ክፍሉን ማጠናከር ላይ እንደማተኮሩ ለተሰላፊነት ፉክክር ይጠብቀዋል።

ሮቤል አስራት ሌላው የወልዋሎ ፈራሚ ነው። ጅማ አባ ጅፋር ወደ ፕሪምየር ሲያድገ ድንቅ የውድድር ዓመት ያሳለፈው ሮቤል በክረምቱ ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርቶ የነበረ ቢሆንም የተጠበቀውን ያህል የመሰለፍ እድል ሳያገኝ ውሉ ሳይጠናቀቅ ነበር ከክለቡ ጋር የተለያየው። በወልዋሎ ለአንድ ዓመት የፈረመው ሮቤል ከሌላው አዲስ ፈራሚ ብርሀኑ ቦጋለ ጋር ለግራ ተከላካይ ስፍራ ይፎካከራል።

ወልዋሎ የዝውውር መስኮቱ ከተከፈተ ወዲህ የሁለቱን ጨምሮ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ቁጥር 8 ደርሷል።