ይሁን እንዳሻው የጅማ አባጅፋር ወይስ የወልዋሎ ?

ይሁን እንደሻው በጅማ አባጅፋር ውሉን አራዝሟል ቢባልም ወልዋሎም ማስፈረማቸውን መግለፃቸውን ተከትሎ ጉዳዩ አደናጋሪ ሆኗል።

ከሰዓታት በፊት ይሁን እንዳሻው ወደ ወልዋሎ ማምራቱን መግለፃችን ይታወቃል። ተጫዋቹም ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ከጅማ ጋር በውል ማራዘምያ ዙርያ ባለመስማማቱ ወደ ወልዋሎ ስለማምራቱ ገልፆ ነበር። ሆኖም አሁን ደግሞ ከጅማ አባ ጅፋር ባገኘነው መረጃ መሰረት የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ወደ ወልዋሎ የሚያደርገውን ዝውውር በመተው በጅማ ለመቆየት መስማማቱ ተገልጿል። 

በጉዳዩ ዙርያ የወልዋሎ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም “ተጫዋቹ ጠዋት አስፈርመነዋል። የአንድ ዓመት ውል ተዋውለን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አስገብተን አፀድቀናል። አሁን ላይ ጅማ ውሉን አድሷል ሲባልም ሰምተናል። ተጫዋቹ እኛ ጋር ፈርሞ ሳለ ወደ ሌላ መሄዱን አንቀበልም። በቀጣይ የተገቢነት ክሳችንን ለፌዴሬሽኑ አስገብተን ተገቢን ምላሽ ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን።” ብለዋል፡፡

በጅማ በኩል  ደግሞ ስራ አስኪያጁ አቶ እስከዳር ዳምጠው እንዲህ ብለዋል። ” ተጫዋቹን እኛ አስፈርመነዋል። ውሉንም ማደሱን በፊርማ አረጋግጦልናል። ተጫዋቹ ስለዚህ ህጋዊ ተጫዋቻችን ሆኗል፤ ለሚመጡት ጥያቄዎች ግን በህጉ መሠረት በመረጃ አስደግፈን ማቅረብ እንችላለን” ብለዋል፡፡