ታንዛንያ 2019 | ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የማጣርያ ዝግጅቱን ቀጥሏል

በታንዛንያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2019 የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታውን በሴካፋ ዞን የሚያደርገው የኢትዮጵያ 17 ዓመት በታች ቡድን በሀዋሳ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል።

በታንዛኒያ በሚካሄደው የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድር ከነሃሴ 4-20 በዋናው ውድድር አስተናጋጅ ታንዛንያ ይደረጋል። በተመስገን ዳና የሚመራው ቡድንም ከሀምሌ 25 ጀምሮ በሀዋሳ ከትሞ በሰው ሰራሽ ሳር ላይ ልምምድ በማድረግ ላይ ይገኛል።

በባቱ ሲደረግ በነበረው ከ17 ዓመት በታች የማጠቃለያ ውድድር ላይ አስቀድሞ ለ41 ተጫዋቾች ጥሪ ተደርጎላቸው የነበረ ቢሆንም በMRI ውጤት ሰባት ተጫዋቾች ብቻ ሲያልፉ ቀሪዎቹ በመውደቃቸው ምክንያት በድጋሚ ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ 13ቱ አልፈው በጥቅሉ 20 ተጫዋቾችን ተለይተዋል። ቡድኑ በአዲስ አበባ አስቀድሞ ልምምዱን ለመስራት እቅድ የነበረው ቢሆንም የተጫዋቾቹ የMRI ምርመራ ሒደት በታሰበው ቀን ልምምዳቸውን መጀመር እንዳይችሉ አድርጎቸው ሰንብቷል።


ያለፉትን አራት ቀናት መሰረታዊ ተግባራት ላይ ያተኮሩ ልምምዶችን ሲሰሩ የተስተዋለ ሲሆን ቡድኑ በቂ የልምምድ ጊዜ አለማግኘቱ ስጋት የሚፈጥር ጉዳይ ሆኗል። በሴካፋ ውድድር በተሰራ የፓስፖርት ስህተት በጊዜ ከውድድሩ ውጭ የሆነው ቡድኑ ይህ ስህተት ዳግም እንዳይፈጠር አስቀድሞ ጥንቃቄ ማድረጋቸውን ፌድሬሽኑ አስታውቋል፡፡
ስለዝግጅታቸው እና ስለውድድሩ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን ያደረገው የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና የተሻለ ውጤትን ይዞ ወደ አህጉራዊው ውድድር ለመግባት የሚቻላቸውን ለማድረግ ማሰባቸውን ተናግሯል” ልምምድ ከጀመርን በትክክል ሶስተኛ ቀናችን ላይ ነን። ጊዜያችንን የጨረስነው በMRI ምርመራ እና በተጫዋቾች ምልመላ ላይ በመሆኑ ባሰብነው ሰዓት ልምምድ መጀመር አልቻልንም።”  የሚለው አሰልጣኙ ብሩንዲ ላይ በተፈጠረ ስህተት ከውድድሩ ውጭ የሆነው ብሔራዊ ቡድኑ ዳግም ስህተት እንዳይፈጠር እንደተሰራም አክሎ ገልጿል። “በትክክል የተጫዋቾቹን ዕድሜ የመረመርን ሲሆን በዋነኛነት እስከ 2019 የመጫወት ተገቢነት ያላቸው ተጫዋቾችን ነው የመረጥነው። በዚህም አጋጣሚ ተገቢ እድሜ ላይ መሆናቸውን MRI በሚገባ አጣርቶ የተገኙ በመሆናቸው ስህተት ይፈጠራል የሚል እምነት የለኝም” ብሏል፡፡

ተመስገን በመጨረሻም በውድድሩ ላይ ያለውን እቅድ ገልጿል፡፡ ” ዋንጫ እናነሳለን ብይ ስሜታዊ መሆን አልፈልግም በጥብቅ እድሜ ምርመራ አድርገን ትክክለኛ ያልናቸውን ልጆች ነው ያካተትነው በኛ ደረጃ ያሉ ቡድኖች በትክክለኛ ዕድሜ ያሉ ልጆችን ካመጡ የተሻለ ውጤት እንደምናመጣ መናገር እችላለሁ በትክክል የዕድሜ ገደብ የሌላቸው ካሉ ግን በስሜት ዋንጫ እናመጣለን ማለት ከባድ ነው። ” ብሏል።

ብሔራዊ ቡድኑ ነገ ከሀዋሳ ከተማ ከ15 ዓመት በታች ቡድን ጋር የዝግጅት ጨዋታ የሚያደርግ ሲሆን የፊታችን ማክሰኞ ውድድሩ ወደሚደረግበት ታንዛንያ የሚያቀና ይሆናል ፡፡


ወደ ታንዛኒያ የሚያመሩ የመጨረሻ 20 ተጫዋቾች

ግብ ጠባቂዎች: ስጦታው አበበ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አላዛር ማርቆስ (ሀዋሳ ከተማ )፣ ኪሩቤል ኃይለ (ኤሌክትሪክ)

ተከላካዮች፡ ረጂብ ሚፍታ (ማራቶን)፣ ያሬድ ማቲያስ (ሀዋሳ)፣ በረከት ካሌብ (ሀዋሳ)፣ አማኑኤል ተረፊ (ቅዱስ ጊዮርጊስ )፣ ናኦል ተስፋዬ (ከስዊድን)


አማካዮች
፡ ወንድማገኝ ኃይሉ (ሀዋሳ ከተማ)፣ ሙሀባ አደም (ሲዳማ ቡና)፣ አቤል ዮናስ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ሮብሰን ደምሰው (አፍሮ ጽሆን)፣ ሐብቶም ወልዱ (አካዳሚ)፣ ኪሩቤል አከለ (ሀዋሳ U-15)፣ አሸናፊ አለቴ (መድን) ቢኒያም አይተን (አዳማ)

አጥቂዎች: ምንተስኖት እንድሪያስ (ሀዋሳ ከተማ)፣ በየነ ባንጃ (አፍሮ ጸዮን)፣ ሙሉቀን በቀለ (ሀዋሳ U-15)፣ ከድር ዓሊ ( አካዳሚ U-15)