ሲዳማ ቡና ሁለት ተጫዋቾች አስፈርሟል

የዝውውር ገበያውን ዘግይቶ የተቀላቀለው ሲዳማ ቡና ሁለት ተጫዋቾች ሲያስፈርም የ6 ተጫዋቾችን ውል ማደሱ አስታውቋል። 

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ወላይታ ድቻን በሁለት አመት ኮንትራት ተቀላቅሎ የነበረው ተስፉ ኤልያስ የአንድ ዓመት ውል ከድቻ ጋር እየቀረው በመለያየት ወደ ሲዳማ ቡና በሁለት ዓመት ኮንትራት አምርቷል።

ዓመቱን በሁለት ክለቦች ያሳለፈው ሰንደይ ሙቱኩም ወደ ሲዳማ ቡና ተመልሷል። በ2009 ከሲሳማ ጋር መልካም ጊዜ አሳልፎ በክረምቱ ወደ ድሬዳዋ ያቀናው ሰንደይ አጋማሽ ላይ ወደ ፋሲል አምርቶ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በአጼዎቹ ቤት ቆይቷል።

ሲዳማ ቡና በክለቡ ያሉ ተጫዋቾችን ውል ያራዘመ ሲሆን ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ፣ ተከላካዮቹ ግሩም አሰፋ፣ ዮናታን ፍሰሀ፣ ሙጃይድ መሀመድ እንዲሁም አማካዮቹ ዮሴፍ ዮሀንስ እና ትርታዬ ደመቀ ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመት ማራዘማቸውን የክለቡ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡