የከፍተኛ ሊግ የዛሬ ውሎ| ሽረ እንደሥላሴ ሁለተኝነቱን አረጋጧል

በአምሀ ተስፋዬ እና ሚካኤል ለገሰ

ትናንት መካሄድ የጀመሩት የከፍተኛ ሊግ የ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲውሉ  ባህርዳር ከተማ አቻ ሲለያይ ሽረ እንደሥላሴ ቢሸነፍም በምድቡ የሁለተኝነት ደረጃን ማሳካት ችሏል።

በርካታ ደጋፊዎች በባህርዳር ኢንተርናሻል ስታደዮም የታደሙበት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቆል።
ኢኮስኮዎች ቀደም ብሎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማለፉን ላረጋገጠው ባህርዳር ከተማ የቡድን አባላት የእንኳን ደስ ያላችሁ አቀባበል አድርገው ጨዋታውን የጀመሩ ሲሆን ባህርዳሮች ከተለመደው አሰላለፍ በርካታ ተጫዋቾችን ለውጠው ወደሜዳ ገብተዋል። በጨዋታውም በመጀመሪያው 15 ደቂቃዋች በእንቅስቃሴ ኢኮስኮች የተሻሉ ነበሩ። አስቀድመው ለግብ የቀረበ ሙከራ ያደረጉት ግን ባህርዳር ከተማዎች ነበሩ። ሆኖም በ19ኛው ደቂቃ የኋላሸት ሰለሞን በቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ወደግብነት ለውጦ ኢኮስኮን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር ባኋላ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ተቃርበው የነበሩት ኢኮስኮዋች ዕድላቸውን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በ30ኛው ደቂቃ ደግሞ የባህርዳር ግብ ጠባቂ በመጎዳቱ ህመሙ ስለበረታበት ለ4ደቂቃዋች ጨዋታው ተቆርጦ መቀጠሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ክስተት ነበር።

በዕረፍት ሰዓት የባህርዳር ደጋፊዎች ለአሰልጣኝ ጳውሎስ እንዲሁም ለምክትል አምበሉ ፍቅረሚካኤል ስጦታ አበርክተዋል። ከእረፍት መልስ ወደ ሜዳ ተቀይረው የገቡት ግርማ ዲሲሳ እና ፍቃዱ ወርቁ በቡድኑ እንቅስቃሴ ወደ ማጥቃት እንዲያደላ አድርገዋል። በተቀራኒው ኢኮስኮ የነበረውን ውጤት አስጠብቆ ለመውጣት የመከላከል አልፌ አልፎ በሚጣሉ ኳሶች ለማጥቃት መጣር መርጧል። በ68ኛው ደቂቃ ወደ ሜዳ ተቀይሮ የገባው ግርማ ደሲሳ ወደ ግብ ክልል ያሻጋረውን ኳስ ፍቃዱ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ለውጦታል። ከግቡ በኋላ መነቃቃት ያሳዩት ባህርዳሮች በ78ኛው ደቂቃ መሪ መሆን የሚችሉበትን የግብ ዕድል በሙሉቀን ታሪኩ አግኝተው ግብ ጠባቂው አድኖባቸዋል። ኢኮስኮዎች ጥሩ በተንቀሳቀሱባቸው የመጨረሻዋቹ ደቂቃዋች አበበ ታደሰ እና ሙሴ ተክለወይኒ ለኢኮስኮ የግብ አጋጣምዎችን ፈጥረዋል።

የካ ክፍለ ከተማን እና ሽረ እንደስላሴን በኦሜድላ ሜዳ ያገናኘው ጨዋታ በየካዎች አንድ ለምንም አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ባለ ድሎቹን ከወራጅ ቀጠናው ስጋት በመጠኑም ቢሆን እንዲርቁ አድርጓቸዋል።
ይጀመራል ተብሎ ከተጠበቀበት ሰዓት 30 ያክል ደቂቃዎችን አርፍዶ በጀመረው ጨዋታ ሽሬዎች ከጨዋታው ከተቻለ ሶስት ነጥብ ካልተቻለ ደግሞ አንድ ነጥብ አግኝቶ የምድቡ ሁለተኛ ሆኖ ለማጠናቀቅ እና በቀጣይ አመት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመሳተፍ ወደ መለያው ጨዋታ ለማለፍ እንዲሁም የካዎች ካሉበት የወራጅ ቀጠና ስጋት ለመውጣት የሚደረግ ፉክክር እንደመሆኑ ጥሩ ጨዋታ ይታያል ተብሎ የተጠበቀ ሲሆን ሽሬዎች ደከም ያለ የካዎች  ደግሞ የተሻለ እንቅስቃሴ አሳይተውበታል።

የጨዋታው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ሽረዎች ወደ የካ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉ ሲሆን  በተለይ ቡሩክን የመጨረሻ ኢላማቸው አድርገው ኳሶችን ለእርሱ በመስጠት ሙከራዎችን ሲያደርጉ ታይቷል። በ12ኛው ደቂቃ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ የተደረገ ሲሆን ቡሩክ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ በሚገባ ተቆጣጥሮት ብቻውን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ አጋጣሚውን ሳይጠቀምበት በግብ ጠባቂው መክኖበታል። በ28ኛው ደቂቃም ልደቱ ለማ ለሳሙኤል ተስፋዬ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ሳሙኤል በሚገባ ባለመምታቱ የካዎች መረብ ላይ ማረፍ ያልቻለች ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ከተገኙ አስቆጪ አጋጣሚዎች ተጠቃሽ ነበሩ። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የገቡት የካዎች በፍጥነት ክፍተቶቻቸውን በማረም የተሻለ የተንቀሳቀሱ ሲሆን በተለይ ዮናስ እና በኃይሉ ለቡድናቸው ጥሩ ጥሩ የግብ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ታይቷል። በ31ኛው ደቂቃም በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሽረዎች የግብ ክልል በቀላሉ የደረሱ ሲሆን በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ዮናስ ሰለሞን ለአሸናፊ ካሳ አቀብሎት ያመከናት አጋጣሚ አስደንጋጭ ነበረች። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም የካዎች የቅጣት ምት አግኝተው የመስመር ተከላካዩ ንጉስ ጌታሁን በግንባሩ በመግጨት ሙከራ ያደረገ ሲሆን ኳሷ ሀይል ስላልነበራት ግብ ጠባቂው በቀላሉ ተቆጣጥሯታል። ኳሶችን አደራጅተው ለመጫወት ሲሞክሩ የነበሩት ሽረዎች በሜዳው ጭቃማነት ምክንያት ብዙ ኳሶችን ያበላሹ ሲሆን ከሜዳው ጋር ለመስማማትም ሲቸገሩ ተስተውሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሽረዎች በመጠኑም ቢሆን የአጨዋወት ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ብቸኛ የፊት አጥቂ የነበረውን ብሩክን ወደ መስመር በማውጣት ልደቱን ወደ መሃል አስገብተው የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም ኳሶችን ወደ መስመር እያወጡ ሲጫወቱ ተስተውሏል። ከእረፍት በፊት መነቃቃት ያሳዩት የካዎች አሁንም  ጫና ማሰደራቸውን ቀጥለው በ51ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ዮናስ በግል ጥረቱ ከረጅም ርቀት ተጨዋቾችን እያለፈ ወደ ተጋጣሚ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል መድረስ የቻለ ሲሆን ወደ ግቡ የመታት ኳስ ግን ኢላማዋን ስታ የግቡን ቋሚ ታካ ወደ ውጪ ወጥታለች። በጨዋታው ብልጫ የተወሰደባቸው ሽረዎች የተጨዋች ቅያሪዎችን አድርገው ወደ እንቅስቃሴው ዳግም ለመግባት ጥረት ያደረጉ ሲሆን የየካዎችን የማጥቃት አጨዋወት ግን በሚገባ ማስቆም አልቻሉም። በ70ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አለማየሁ አባይነህ ከተከላካዮች ጀርባ በመሮጥ ከበኃይሉ ሀ/ማርያም የተሻገረለትን ኳስ በሚገባ ተቆጣጥሮት ወደ ግብ የመታት ሲሆን ኳሷ ወደ ላይ በመውጣት ጎል ሳትሆን ቀርታለች። ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉት  የካዎች አሁንም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቀላሉ እየደረሱ ኳሶችን እያመከኑ የቀጠሉ ሲሆን በ72ኛው ደቂቃ ግን የልፋታቸውን ፍሬ አግኝተዋል። ከግራ መስመር ዮናስ ያሻማውን ኳስ የሽሬው የመሃል ተከላካይ እና አምበል የሆነው መብራህቶም ፍሰሀ የሜዳው ጭቃ አንሸራቶት በራሱ መረብ ላይ ጎል አስቆጥሮ የካዎች መሪ መሆን ጀምረዋል። ከግቡ መቆጠር በኃላ ሽረዎች አቻ ለመሆን ከቅጣት ምት እና ከርቀት የሚያገኟቸውን አጋጣሚዎች ለመጠቀም ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይም የካዎች የጎሉን ልዩነት የሚያሰፉበትን አጋጣሚ በአለማየሁ እና በበኃይሉ አማካኝነት አግኝተው የነበረ ሲሆን ዕድላቸውን ግን ሳይጠቀሙበት በአንድ የግብ ልዩነት ብቻ አሸንፈው ወጥተዋል።

ሽረዎች ምንም እንኳን ከጨዋታው ነጥብ ማግኘት ባይችሉም አዲስ አበባ ከተማ ነጥብ በመጋራቱ ምድቡን በሁለተኝነት ማጠናቀቁን ረጋግጧል። በቀጣይም ከምድብ ለ በተመሳሳይ በሁለተኝነት ከሚጨርሰው ቡድን ጋር በመጫወት ወደ ፕሪምየር ሊጉ የመግባት ዕድሉን የሚወስን ይሆናል።

በሌሎች ጨዋታዎች ፌዴራል ፖሊስ ኦሜድላ ሜዳ ላይ አውስኮድን 2-0 በማሸነፍ ከአደጋው ዞን ፈቀቅ ሲል ወሎ ኮምቦልቻ በሜዳው ከለገጣፎ አቻ ተለያይቶ ወደ ወራጅ ቀጠናው ተመልሷል። አዲስ አበባ ከተማ ከደሴ ከተማ 2-2 የተለያዩበት ጨዋታም የዛሬ መርሀ ግብር ነበር።