የካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ ትላንት ምሽት አዲስ አበባ ገብተዋል

ለረጅም አመታት የአፍሪካ እግር ኳስ ሲመሩ የነበሩትን አንጋፋው ኢሳ አያቱን ከአንድ ዓመት በፊት አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ምርጫ በማሸነፍ የስልጣን በትሩን የያዙት አህመድ አህመድ ወደ ስልጣናቸው ከመጡ በኃላ በርካታ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ።

ፕሬዝዳንቱ በአህጉሪቱ የሚደረጉ ውድድሮች ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ አዳዲስ ደንቦችን ከማምጣት ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም በ2020 የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) እንደምታስተናግድ የሚታወቅ ሲሆን ስለ ቅድመ ዝግጅቱ እና ስለ መደረግ ስላለባቸው ሁኔታዎች ፕሬዝዳንቱ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ጋር ንግግር እንደሚያደርጉ ተነግሯል።

አራት ስታዲየሞች በዋነኝነት ለዚህ  ውድድር እንደሚዘጋጁ የሚጠበቅ ሲሆን ይመረጣሉ ተብለው የሚጠበቁት የባህርዳር፣ ሃዋሳ፣ መቐለ እና አደይ አበባ ስታዲየሞች የግንባታ ሁኔታ ግን እስካሁን አልተጠናቀቀም። እነዚን ጉዳዮችን ጨምሮ መንግስት ለውድድሩ ምን ማድረግ እንዳለበት በሚጠቁሙ ሃሳቦች ላይ ፕሬዝዳንቱ ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን በአዲስ አበባም የሁለት ቀን ቆይታ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።

በዋነኝነት ግን ፕሬዝዳንቱ ሲ ኤም ሲ አካባቢ የሚገኘውን እና ካፍ ለምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ያስገነባውን የልዕቀት ማዕከል(center of excellence) ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለመስረከብ መምጣታቸው የታወቀ ሲሆን ከሁለት ሳምንታት በፊት በቃል ብቻ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ተቋሙን እንዲያስተዳድር የተገለፀውን ስምምነት በይፋ ፕሬዝዳንቱ እንዲያከናውኑት ነው ተብሏል።

አህመድ አህመድ ከዚህ ቀደም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ጋር ስለ አፍሪካ እግር ኳስ ህዳሴ ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን የካፍ የልዕቀት ምዕከልን እና የኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚን መጎብኘታቸውም ይታወሳል።