ድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያ ተጨዋቹን አስፈርሟል

የኢትዮጵያ የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ከተከፈተ በኋላ በርካታ ክለቦች በስፋት በዝውውሩ ላይ እየተሳተፉ ሲገኙ ዝምታን ከመረጡ ሶስት ክለቦች አንዱ የሆነው ድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያ ተጨዋቹን አስፈርሟል።

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን ወደ ቡድናቸው ያመጡት ድሬዎች በዝውውሩ ላይ እስካሁን አለመሳተፋቸው አግራሞትን የፈጠረ ነገር ቢሆንም አሁን አንድ ተጨዋች የግላቸው አድርገዋል። ንግድ ባንክን ከለቀቀ በኋላ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ከመቐለ ከተማ ጋር ያሳለፈው ፍቃዱ ደነቀ ወደ ድሬዎች ቤት በሁለት ዓመት ውል ማምራቱ ሲረጋገጥ ተጨዋቹም ከቀድሞ አሰልጣኙ ጋር ዳግም አብረው የሚሰሩበት እድል ተፈጥሯል።

ቡድኑ አዳዲስ ተጨዋቾችን ከማምጣት ጎን ለጎን የነባር ተጨዋቾች ውል እያደሰ እንደሚገኝ ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ሲጠቁም የተከላካይ መስመር ተጨዋቹ በረከት ሳሙኤልን ከቡድኑ ጋር ለመቀጠል ውል አድሷል።

በ2009 ዓም የክረምቱ የዝውውር መስኮት በርካታ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ ሲያመጣ የነበረው ድሬዳዋ ከተማ ዘንድሮ በዝውውሩ  ብዙም እንቅስቃሴ አለማድረጉ አስገራሚ የሚመስል ቢሆንም ከዚህ በኃላ ግን ከቡድኑ የለቀቁ ተጨዋቾችን ለመተካት እና በአመቱ የነበሩበትን ክፍተቶች ለመሸፈን አዳዲስ ተጨዋቾችን ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።