አዳማ ከተማ ሶስተኛ ተጨዋች አስፈርሟል

በቅርብ ዓመታት ጠንካራ ፉክክር እያደረገ በተከታታይ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ የቆየው አዳማ ከተማ ዘንድሮ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን በቀጣይ ዓመት ወደ ዋንጫው ፉክክር ዳግም ለመመለስ የአሰልጣኝ ቅጥር ከማድረግ ጀምሮ ተጫዋቾችን እያስፈረመ ይገኛል።

አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽን በማንሳት ሲሳይ አብርሃምን የቀጠረው ቡድኑ በትላንትናው እለት ሶስተኛ ተጨዋቾችን ማስፈረሙ ታውቋል። በባህርዳር ከተማ ዘንድሮ ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው የፊት መስመር አጥቂው ሙሉቀን ታሪኩ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሶ ለአዳማ ከተማ የሁለት ዓመት ውል ሲፈራረም በባህርዳር ከተማ የነበረው ቆይታ በመጠናቀቁ እና ውሉን እንዲያራዝም ከክለቡ ጥያቄ አለመቅረቡን ተከትሎ አዳማን ለመቀላቀል እንደወሰነ ተጨዋቹ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።

ሙሉቀን ከባህርዳር ከተማ በፊት በአዳማ ከተማ፣ አውስኮድ እና ፋሲል ከነማ መጫወቱ የሚታወስ ሲሆን በአዳማ በነበረው ቆይታ ከአዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ ሲሳይ ጋር አብረው መስራታቸው ይታወቃል። አዳማዎች ከዚህ ቀደም ቴዎድሮስ በቀለ እና ሱራፌል ዳንኤልን ማስፈረማቸው የሚታወስ ነው።