ፔትሮጄት በሽመልስ በቀለ ጎሎች የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ድል አሳክቷል

የ2018/19 የግብፅ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት መደረግ ሲጀምሩ ፔትሮጄት በሽመልስ በቀለ ጎሎች 2-0 በማሸነፍ ሊጉን በጊዜያዊነት መምራት ጀምሯል። 

አርብ ምሽት ወደ ካይሮ ሚሊተሪ አካደሚ ስታድየም አቅንቶ ዋዲ ደግላን የገጠመው ፔትሮጄት 2-0 አሸንፏል። ቡድኑን በአምበልነት እየመራ የሚገኘው ሽመልስ በቀለ በ38ኛው እና 42ኛው ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው ጎሎች ፔትሮጄት የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ድል ማሳካት ሲችል ሊጉንም በ5 ነጥቦች በጊዜያዊነት መምራት እንዲችል አድርጎታል። 

የ4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ሲቀጥሉ ኡመድ ኡኩሪ እየተጫወተበት የሚገኘው ስሞሀ ከኤል ጋይሽ ጋር እሁድ ይጫወታል። ጋቶች ፓኖም የሚገኝበት አዲስ አዳጊው ኤል ጎውናም በተመሳሳይ እሁድ ከሜዳው ውጪ ኤል ኤንታግ አል ሀርቢን ይገጥማል።