አስተያየት | ፌዴሬሽኑ ከካፍ የተረከበው የልህቀት ማዕከል ፋይዳ..

አስተያየት – በሚካኤል ለገሰ

በዓለም እግር ኳስ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች እና አህጉራዊ ፌደሬሽኖች ለእግር ኳሳቸው እድገት ዕለት ይተጋሉ። በተለይም በወጣቶች እና ተተኪ ታዳጊዎች ላይ ሰፋፊ ስራዎችን በዕቅድ ሲያከናውኑ ይታያል፡፡ ወጥ የሆኑ የስልጠና አሰጣጥ መንገዶችን ከመቀየስ ጀምሮ የልህቀት ማዕከላትን እስከማስገንባት እና ጥቃቅን እስከሚባሉ ዝርዝር ጉዳዮች ድረስ ትኩረት በማድረግ የእግር ኳስ ደረጃቸውን ለማሳደግ የሚጥሩ ሲሆን በአስተማማኝነት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ትውልድ በማፍራት ላይም ያተኩራሉ።

ለዚህ ጉዳይ ያልታደለች የምትመስለው አፍሪካ በመርህ ደረጃ ሃሳቡን ብትቀበለውም ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት ግን ማመንታት ይታይባታል፡፡ ለረጅም አመታት በኢሳ ሀያቱ ሲመራ የነበረው የአፍሪካ እግር ኳስ በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚችል ስኬት ያላስመዘገበ ሲሆን የአህጉሪቷን እግር ኳስ ለማሳደግ ጠንካራ ስራዎች አለመሰራታቸውን መናገር ይቻላል፡፡

የፅሁፋችን መነሻ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሲ ኤም ሲ አካባቢ የሚገኘውን የልህቀት ማዕከል ለማስተዳደር ከካፍ መረከቡ ሲሆን ኢትዮጵያም ከዚህ ጉዳይ ልታገኝ የምትችላቸውን ጥቅሞች እና ፌደሬሽኑ ሊሰራ ስለሚገባቸው ስራዎች ለመጠቆም እንሞክራለን።

ካፍ የመጀመሪያውን የልህቀት ማዕከል በካሜሩን ምባንኮሞ ከተማ (ከዋናው ከተማ ያውንዴ 30 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ) አስገንብቶ በግንቦት 2014 በቀድሞዎቹ የካፍ እና የፊፋ ፕሬዝዳንቶች ኢሳ አያቱ እና ሴፕ ብላተር አስመርቋል፡፡ ይህ ማዕከል ግንባታው ረጅም ጊዜ የፈጀ ሲሆን ካፍ ግንባታው የሚከናወንበትን ቦታ ከካሜሩን መንግስት በ2004 ተረክቦ በመጠኑ አነስተኛ የሆነ ማዕከል ገንብቶ ነበር። ማዕከሉ ለካሜሩን እግር ኳስ ፌደሬሽን በርካታ የዕድል በሮችን በመክፈት እስካሁን ድረስም አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ካፍ በመቀጠል ኢትዮጵያ እና ሴኔጋል ላይ ተጨማሪ ማዕከሎችን ያስገነባ ሲሆን እንደ ካሜሩኑ ሁሉ እነዚህም ግንባታቸው ረጅም ጊዜ ፈጅቷል፡፡ በሴኔጋል ጉሬዎ ከተማ (ከዋና ከተማው 77 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ) የተገነባው ማዕከል ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ባይጠናቀቅም ስራ ላይ መዋሉ ይታወቃል። ከሶስት ሳምንታት በፊትም የካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ ሴኔጋልን በሚጎበኙበት ወቅት የሴኔጋል እግር ኳስ ማህበር ማዕከሉን እንዲያስተዳድር ርክክብ አድርገዋል፡፡ እንደ ሴኔጋል እና ካሜሩን ይህንን ዕድል ያገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አጋጣሚውን በአግባቡ ከተጠቀመበት ለሀገራችን የእግር ኳስ ዕድገት መጠነኛ ለውጥ እንደሚያመጣ ተስፋ ተጥሎበታል። በአህጉሪቱ ሶስተኛ የሆነው ይህ የልዕቀት ማዕከል በውስጡ ብዙ የእግር ኳስ ተጨዋቾችን ሊያስተናግድ እንደሚችል የሚጠበቅ ሲሆን የቤት ውስጥ እና ከቤት ውጪ የሚደረጉ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ሊያሰሩ የሚችሉ ቦታዎችም አሉት፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ለስፖርተኞቹ ማረፊያነት የሚያገለግሉ ክፍሎችንም ይዟል።

ማዕከሉ ግንባታው ሳይጠናቀቅ ብልሽቶች እየታዩበት ይገኛል

የልዕቀትት ማዕከላት ለአንድ ሀገር የእግር ኳስ ዕድገት የራሳቸው የሆነ ጠቃሚ ጎኖች ያሏቸው ቢሆንም ከፍተኛ ብቃት ያላቸው አስተዳደሪዎችን ይሻሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በዋነኝነት ይህንን ማዕከል እንዲመራ ሲደረግ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ዕድገት ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካ ሃገራትም ጭምር መሆኑ ታውቆ በዞኑ የእግር ኳስ መነቃቃቶች እንዲኖሩ በማሰብ ነው ካፍ ከ14 ዓመታት በፊት ግንባታውን የጀመረው፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ይህንን ማዕከል ለማስተዳደር በቁርጠኝነት መወሰኑ እና መረከቡ ትልቅ እርምጃ ቢሆንም ፌደሬሽኑ ካሉበት ተደራራቢ ስራዎች አንፃር ኃላፊነቱ ሊከብደው እንደሚችል ይገመታል፡፡ የአንድ ሀገር ብሔራዊ ፌዴሬሽን በዋነኝነት በየእርከኑ የሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖችን መከታተል እና የእግር ኳስ የልማት ስራዎች ማስፋፋት ሊሰራቸው የሚገቡ ዋነኛ ስራዎች ሲሆኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ግን ሁሉንም በሃገሪቱ የሚገኙ ሊጎችን መምራት እና በሃገሪቱ የሚደረጉ ውድድሮችን ማብዛት እንደ ቀዳሚ ስራው በማድረግ ዋነኛ ስራዎቹን የረሳ ይመስላል፡፡ ፌደሬሽኑ ከላይ የተጠቀሱ ስራዎችን በመስራት የተጠመደ በመሆኑ አሁንም የማዕከሉ ህልውና ላይ ስጋቶች እንዳይኖሩ እና አዲሱ የስራ አስፈፃሚ ገና ከመምጣቱ ፈታኝ ነገሮች እንዳይገጥሙትም ያሰጋል፡፡ ይህን ችግር  ለመፍታት ፌደሬሽኑ ራሱን ለልዕቀት ማዕከሉ ማዘጋጀት እንዳለበት ተጠሪነቱ ለፌደሬሽኑ የሆነ ጠንካራ ልምድ ያለው ራሱን የቻለ አስተዳዳሪ  ቡድን ማቋቋም እንዳለበት ይታመናል፡፡ ማዕከሉ በጀት የሚለቀቅለት በፌደሬሽኑ በኩል ይሁን እንጂ ሙሉ ለሙሉ በትኩረት የሚያስተዳድረው አካል የሚፈልግ በመሆኑ በዋነኝነት ራሱን ችሎ እንዲቆም መድረግ አለበት፡፡

የማዕከሉ ግንባታ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ባይጠናቀቅም በአጭር ጊዜ የፊኒሺንግ እና ተያያዥ ስራዎችን በማገባደድ ስራ ላይ መዋል ይችላል። ነገር ግን ከተጠናቀቀ በኋላ በማዕከሉ የሚሰጡ ስራዎችን ለይቶ ማስቀመጥ ይገባል፡፡ በዋነኝነት ማዕከሉ ለብሔራዊ ቡድኖቻችን ጥሩ ዜናን ይዞ እንደሚመጣ ሲጠበቅ በተለይ በሁለቱም ፆታዎች በየዕርከኑ የሚገኙ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድኖቻችን መሰረት መሆን ይገባዋል፡፡በሃገራችን እንደ ልምድ ሆኖ የቀረው የታዳጊ ብሄራዊ ቡድኖቻችን ለውድድር ጊዜ ብቻ መሰብሰብ ለረጅም ጊዜ ቡድናችንን እንዳንገነባ እያደረገን መሆኑ የሚታይ ሲሆን በየጊዜው ተጨዋቾችን እየሰበሰቡ ተከታታይ ስልጠናዎችን ለመስጠት ማዕከሉ ጠቃሚ ነው፡፡

ማዕከሉ በቂ የማረፍያ ክፍሎች ያሉት በመሆኑ ለብሔራዊ ቡድኖች ዝግጅት ሊያገለግል ይችላል

ይህ ማዕከል ለታዳጊዎች ብቻ ሳይሆን ለዋናው ብሔራዊ ቡድናችንም እንደ ካምፕነት ማገልገል ይችላል። ፌደሬሽኑ ውድድሮች ባሉበት ወቅት የሚያወጣውን የሆቴል ወጪ በቋሚነት ሊቀንስለትም ይችላል፡፡ በሀገሪቱ መሰረተ ልማት የተሟላለት የልምምድ ሜዳ አለመኖሩ ይህን ማዕከል በእግርኳሱ የተሻለ ደረጃ የደረሱ ሀገሮችን ልምድ በመውሰድ ወደ ቴክኒክ ማዕከልነት ለመቀየር መነሻ ሊሆን ይችላል። አንድ ቡድን ዝግጅት ላይ ሲሆን ተጨዋቾቹ ሙሉ ለሙሉ ትኩረታቸውን መሰብሰብ ያለባቸው በመሆኑ ሁሉንም ነገሮች በአንድ ቦታ ያሟላ ማዕከል ያስፈልጋቸዋል። በሆቴሎች በመቀመጥ የሚደረጉ ዝግጅቶች አድካሚ እና ወጪ የሚያስወጡ ከመሆናቸው በተጨማሪ በሆቴሎች የሚገኙ የመዝናኛ ከአማራጮች የተጫዋቾችን ትኩረት የሚሰርቁ ናቸው። እነዚህና መሰል ችግሮችን ለመፍታትም ማዕከሉ የጎላ ሚና ይኖረዋል።
ሌላው ማዕከሉ የተለያዩ ስልጠናዎች የሚሰጡበት ቦታ መሆን ይጠበቅበታል። ብዙ ጊዜ በሃገራችን የሚጠቀሰው ታዳጊዎችን የማፍራት ጉዳይ ቢሆንም ከዛ በፊት እነዚህን ታዳጊዎች የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች መብቃት እንዳለባቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ በአጫጭር ኮርሶች የሚሰጡ የተለያዩ የአሰልጣኝነት ስልጠናዎች ለእግርኳሳችን በቂ እንዳልሆነ ተገንዝበን ወጥ በሆነ መልኩ በተመሳሳይ ካሪኩለም ለሁሉም አሰልጣኞች በዕኩል ደረጃ ለመስጠት የማዕከሉ መኖር አመቺ ነው፡፡ ማዕከሉ ቡድኖችን በዋናነት ከሚመሩ አሰልጣኞች በተጨማሪ በውጪ ሃገራት እንደምንመለከተው የተለያዩ ሚና ያላቸውን የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን ለማፍራትም እንዲሁ ጠቃሚ ነው፡፡ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ፣ የአካል ብቃት አሰልጣኝ ፣ የተጨዋቾች መልማይ ፣ የተጋጣሚ ቡድን አጥኚ እና ሌሎች ባለሙያዎችን በብዛት ለማፍራት ይረዳል፡፡ ከአሰልጣኞች እና ተጨዋቾች በተጨማሪ ማዕከሉ የዳኞችንም ስልጠና በማከናወን ከካፍ እና ፊፋ ከሚሰጡ ስልጠናዎቸ ውጪ አዳዲስ እና ተተኪ ዳኞችን በመደበኛ መርሐ ግብር ለማፍራት እዚሁ ሃገር ውስጥ በየደረጃው ስልጠናዎችን መስጠት ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ ማዕከሉ የላቁ የእግርኳስ ሰዎችን በወጥነት በየዓመቱ ለማፍራት ከታሰበ የእግር ኳስ ትምህርቶችን በዘመናዊ መልኩ ለመስጠት ቅድሚያ ጥናቶች ተደርገው በማዕከሉ የሚሰጡ ስልጠናዎች በምን አይነት መልኩ ሊሆኑ እንደሚገባቸው የሃገራችንን ተጨዋቾች ታሳቢ ያደረገ ወጥ ካሪኩለም ሊወጣለት ይገባል፡፡ በመቀጠል በቀጥታ ጊዜ ሳይወሰድ ማዕከሉ ስራ እንዲጀምር መደረግ ይኖርበታል። ያላለቁ ስራዎች ቶሎ እንዲያልቁ እና አገልግሎት ላይ ሳይውሉ የተበላሹትንም በቶሎ እንዲስተካከሉ በማድረግ ማዕከሉ ወደ ስራ እንዲገባ ቢደረግ ጥሩ ይሆናል።