የክልል ክለቦች ሻምፒዮና የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት ተከናውኗል

ወደ አንደኛ ሊግ ለማደግ ከነሀሴ 6-21 በሀዋሳ የሚደረገው የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት በሴንትራል ሆቴል ተካሂዷል፡፡

የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓቱን በንግግር የከፈቱት የሀዋሳ ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ታምሩ ታፌ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ክለቦቹ በሚያደርጉበት የውድድር ቦታ እና በሚገኙበት ሁሉ ከስጋት ርቀው ውድድሩን እንዲያካሂዱ አስታውቀዋል። በመቀጠል አቶ ኢሳይያስ ጅራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት ውድድሩ በስፖርታዊ ጨዋነት በሰላም ተጀምሮ እስከ ፍፃሜው እንዲደርስ ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

በመቀጠል አቶ ሰለሞን ገ/ሥላሴ የፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ጸኃፊ የውድድሩን ደንብና መመሪያ ተወክለው ለመጡ የቡድን አባላት፣ ዳኞች እና የቡድን መሪዎች አብራርተዋል። ኢንስትራክተር ይግዛው ብዙዓየው የውድድሩ ሰብሳቢ በመሆን 5 አባላት ያሉት ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን የመስተንግዶ፣ የፀጥታ፣ የሜዳ እንዲሁም የህክምና ኮሚቴ ተመርጠው ክለቦቹ በሀዋሳ በሚኖራቸው ቆይታ ችግሮች እንዳይገጥማቸው ይሰራሉ ተብሏል።

ውድድሩ የሚደረግባቸው ቦታዎች ሀዋሳ የሰው ሰራሽ ሳር ሜዳ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ኮሌጅ እና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ ናቸው ተብሏል። ክለቦቹ ልምምድ የሚያደርጉባቸውም ቦታዎች ላይም ገለፃ ተደርጓል። በውድድሩ ላይ አስቀድሞ 33 ክለቦች ይሳተፋሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም ሁለት ቡድኖች በአንዳንድ ምክያቶች ተቀንሰው 31 ቡድኖች ተካፋይ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ 24 ዳኞች እና 12 ኮሚሽነሮችም ይመሩታልም ተብሏል፡፡

በስተመጨረሻም የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት ተደርጓል።

ምድብ ሀ

ሆለታ ከተማ፣ ጎንደር ውሀ ስራ፣ አንጋጫ ከተማ ወልዋሎ ቢ

ምድብ ለ 

ገርበ ጉራቻ፣  ቆቦ ከተማ፣ አረካ ከተማ፣ ገንፈል ውቅሮ ከተማ

ምድብ ሐ 

አሰላ ከተማ የ፣ ገንደ ውሀ ከተማ፣ ሀደሮ ከተማ፣ መቐለ ከተማ ቢ

ምድብ መ

ኦሮሚያ ፖሊስ፣ ዳንግላ ከተማ፣ ሾኔ ከተማ፣ ቄራ አንበሳ

ምድብ ሠ 

ዶዶላ ከተማ፣ ገንደ ተስፋ ስፖርት፣ መተከል ፓሊስ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ

ምድብ ረ 

ቴክኖ ሞባይል፣ ድሬ ካባ፣ ሶጌ ከተማ፣ ካልዲስ ኮፊ

ምድብ ሰ 

አዲስ አበባ ውሀና ፍሳሽ፣ ዋልያ ስፖርት፣ ግልገል በለስ፣ ሲልቫ ስፖርት

ምድብ ሸ 

ቡሬ ከተማ፣ አንሌሞ ወረዳ፣ መንጌ ቤንሻጉል

ነገ በመክፈቻው ከምድብ ሀ ሁለት ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን በ3:00 አንጋጫ ከተማ ከ ጎንደር ውሀ ስራ በ5:00 ደግሞ ሆለታ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት b ቡድን ጋር በሀዋሳ የሰው ሰራሽ ሳር ሜዳ ላይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።

በዚህ ውድድር ላይ ወደ ሩብ ፍፃሜው የሚሸጋገሩ 8 ክለቦች ወደ 2011 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የሚያድጉ ይሆናል።