አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ስለ ቀይ ቀበሮዎቹ የታንዛንያ ቆይታ ይናገራል

በታንዛኒያ አስተናጋጅነት እየተደረገ ያለው የ2019 የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር የምድብ ጨዋታዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በምድብ 2 ከጅቡቲ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለት ጨዋታዎችን አድርጎ በድል ተወጥቷል።

ቡድኑ በመጀመሪያው ጨዋታ በቻማዚ ስታዲየም ዩጋንዳን ገጥሞ በ68ኛው ደቂቃ ላይ ከሀዋሳ ከተማ የተገኘው አጥቂው ምንተስኖት እንድሪያስ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ሦስት ነጥቦች ማሳካቱ  ይታወሳል። በዚህ ጨዋታ ላይ ዩጋንዳዎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ሌላው ከሀዋሳ ከተማ የተገኘው ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ በመመለስ ለድሉ ወሳኝ ሚና መወጣት ችሏል። ትላንት ደግሞ የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድንን ገጥሞ 4-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል። የአፍሮ ጽዮኑ ቢኒያም ባንጃው፣ ከአዳማ ከተማ የተገኘው ቢኒያም አይተን እና ከሀዋሳ ከ15 ዓመት በታች ፕሮጀክት የተገኘው በረከት ካሌብ በክፍት ጨዋታ ሲያስቆጥሩ ምንተስኖት እንድሪያስ በፍፁም ቅጣት ምት ሌላ ግብ አክሏል፡፡ ቀይ ቀበሮዎቹ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ማለፋቸውን ለማረጋገጥ ነሀሴ 13 ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ የሚጠብቁ ይሆናል።

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ስለ ቡድኑ የእስካሁን ቆይታ፣ ስለ ውድድሩ፣ ስለ ቀጣይ ጨዋታዎች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል።

“ውድድሩ ጠንካራ የሚባል ውድድር ነው። ዝግጅታችን ስድስት ቀናት ብቻ የነበረ ቢሆንም የልጆቹ የመጫወት ፍላጎታቸው እና መነሳሳታቸው የተለየ ነው።” የሚለው አሰልጣኙ ከወራት በፊት  በቡሩንዲ የፓስፖርት ስህተት ያስከተለባቸው ችግር ተስተካክሎ በተገቢ ዕድሜ ውድድር እያደረጉ እንደሆነ ገልጿል። “የኛ ቡድን በትክክለኛ ዕድሜ ተመዝኖ ነው የቀረበው። ለዚህም ይመስላል ኢትዮጵያ ሆነን ካደረግነው የMRI ምርመራ ባለፈ ወደ ታንዛኒያ መጥተን በካፍ ዶክተሮች ምርመራ ተደርጎ ከ9 ሀገራት መካከል የሩዋንዳ ፣ የጅቡቲ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች ብቻ ሁሉም ተጫዋቾች አልፈውላቸዋል። ሌሎች ሀገራት ግን እጅግ በሚያሳፍር መልኩ ከዕድሜያቸው በላይ አምጥተው የተቀነሰባቸው በርካታ ተጫዋቾችን ተመልክቻለሁ። የኛ ቡድን ሁለት ጨዋታ ማሸነፍ ምክንያትም የMRI ምርመራ ውጤቱ ተጨዋቾቼ በነፃነት እና በፍላጎት ከጫና ርቀው እንዲጫወቱ ያስቻለ አንዱ በጎ ጎን ነው። በእድሜ ላይ ለተሰራው ስራ የህክምና ኮሚቴው እና ዶ/ር ነስረዲን ሊመሰገኑ ይገባል።” በማለት ይገልፃል፡፡ 

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በታንዛንያ ቆይታቸው ከሌሎቹ ሀገራት ልምድ ልንቀስማቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ መታዘቡን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት ” ቡሩንዲ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ ረጅም የዝግጅት ጊዜ ነበራቸው። የኛ ቡድን ግን አጭር ጊዜን ነው የተዘጋጀው።  በMRI ምርመራ ችግር ምክንያት ዘግይተን ነው  የጀመርነው። የጅቡቲ ቡድን ከቱኒዚያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታን አድርጎ ነው የመጣው። በተመሳሳይ የኛም ሀገር በእንዲህ አይነት ሂደት መጓዝ ቢቻል ከዚህ ይበልጥ በተሻለ ደረጃ ላይ መገኘት ይቻላል። ሌላው ተጨዋቾቹ ከብሔራዊ ቡድን ባለፈ እየተገናኙ በጋራ መስራት የሚችሉበትን መንገድ መፈጠር አለበት  ብዬ አስባለሁ። ለምሳሌ ቅድም እንዳልኩት እነ ኬኒያ ፣ ጅቡቲ እና ቡሩንዲ ዝግጅታቸው እና ትኩረታቸው ሰፊ ነው። እንደነሱ በተደጋጋሚ ልጆቹን በጋራ ይዘን ለቀጣዩ ብሔራዊ ቡድን መሰረት መጣል አለብን።” ብሏል፡፡

በሴካፋ ዞን ውድድር ላይ ቻምፒዮን የሚሆነው ቡድን ወደ አፍሪካ ዋንጫው የማምራትን ዕድል ያገኛል። የመጀመርያ ሁለት የምድብ ጨዋታቸውን ያሸነፉት ቀይ ቀበሮዎቹም ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ከምድባቸው ከማለፍ በተጨማሪ ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ይጠብቋቸዋል። አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ግን ከወዲሁ ስለዋንጫው ከማሰብ ይልቅ ስለቀጣዩ ጨዋታ ማሰብን እንደሚመርጥ ተናግሯል። ” እኔ ትኩረቴ ቡድኑ ጥሩ ቅርፁን ይዞ ስለመቀጠሉ ነው። አሁን ላይ ሆነን ስለ ዋንጫው ከማውራት ይልቅ ስለቀጣይ ጨዋታ ነው ትኩረት የምናደርገው።” በማለት ሀሳቡን አጠቃሏል።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አርብ በሚደረገው 3ኛ የምድብ ጨዋታ ላይ አራፊ ቡድን ሲሆን ነሀሴ 13 ከደቡብ ሱዳን፣ ነሀሴ 16 ከኬንያ ጋር የሚጫወት ይሆናል።

የደረጃ ሰንጠረዥ

1. ኢትዮጵያ 2 (+5) 6

2. ኬንያ 1 (+4) 3

3. ደቡብ ሱዳን 2 (-2) 3

4. ዩጋንዳ 1 (-1) 0

5. ጅቡቲ 2 (-6) 0