ባህር ዳር ከተማ የማራኪን ዝውውር ሲያጠናቅቅ ዐወትን እንደሚያስፈርም ይጠበቃል

አዲሱ የፕሪምየር ሊግ ክለብ ባህር ዳር ከተማ በዝውውር መስኮቱ አራት ተጫዋቾችን ማስፈረሙ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ከቀናት በፊት በቃል ደረጃ ተስማምቶ የነበረው ማራኪ ወርቁን ሲያስፈርም ዐወት ገብረሚካኤልን ዛሬ ወይም ነገ እንደሚያስፈርም ይጠበቃል።  

ማራኪ ወርቁ በ2007 ሱሉልታ ከተማን በመልቀቅ ወደ መከላከያ አምርቶ ያለፉትን አራት የውድድር ዓመታት በክለቡ የቆየ ሲሆን ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ጣና ሞገዶቹ ማምራት ችሏል። ተጫዋቹ ባለፈው ሳምንት ከክለቡ ጋር ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም በደሞዝ ጉዳይ በነበረ ልዩነት ሳይፈርም ቆይቶ ነበር። አሁን ደግሞ ልዩነቱን በመፍታት የአንድ ዓመት ውል ፈርሟል። ከዚህ ቀደም በሱሉልታ ከተማ አብሮት ከሰራው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ጋር በድጋሚ የሚገናኝም ይሆናል።

ዐወት ገብረሚካኤል ከጣና ሞገዶቹ ጋር ከስምምነት የደረሰ ተጫዋች ነው። የቀኝ መስመር ተከላካዩ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወጣት ቡድን ካደገበት 2004 ጀምሮ እስከተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ድረስ ቆይታ ያደረገ ሲሆን የአንድ ዓመት ውል ቢቀረውም ከኤሌክትሪክ ጋር በስምምነት እንደሚለያይ ተነግሯል። ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በሀዋሳ የሚገኘው ዐወት ዛሬ ወይም ነገ ውል ይፈራረማል ተብሎ ይጠበቃል። ባህር ዳር ከዐወት በተጨማሪ ጃኮ አራፋትን ለማስፈረም በቃል ደረጃ መስማማቱ የሚታወስ ነው።