የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብቷል

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በ2019 ታንዛኒያ ለምታስተናግደው  ከ17 ኣመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታውን በዞን አምስት በታንዛንያ ሲያደርግ ቆይቶ የምድብ ጨዋታውን በአንደኝነት በማለፍ እና የፍፃሜ ግማሽ ጨዋታውን በማሸነፍ ትላንት ለፍፃሜ መድረሱ ይታወቃል። ብሄራዊ ቡድኑ ትላንት በተደረገው የፍፃሜ ጨዋታ በዩጋንዳ 3ለ1 ተሸንፎ ለአፍሪካ ዋንጫው መድረስ ባይችልም በአጠቃላይ በማጣሪያ ውድድሩ ስኬታማ ጊዜ አሳልፏል።

ዛሬ ማለዳ 1 ሰዓት ቦሌ የአየር ማረፊያ የደረሱት በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የሚሰለጥኑት ቀይ ቀበሮዎቹ በቦታው ሲደርሱ ከፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የአበባ ጉንጉን ስጦታ እና የእንኳን ደና መጣችሁ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ስለ ውድድሩ እና ተያያዥ ጉዳዮች አስተያየቱን ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጠ ሲሆን ስለ ተደረገላቸው አቀባበልም ሃሳቡን አጋርቷል።

“ፌደሬሽኑ ያደረገልን አቀባበል መልካም ነው። ከሌሎች ጊዜያት በተለየ ይሄኛው ፌደሬሽን በሚገባ ትኩረት ሰጥቶን ሲከታተለን እና ሲያበረታታን ነበረ። ሌሎች ጊዜያት ውጤት ሲመጣ ብቻ ነበረ ታዳጊዎች ላይ ወሬዎች የሚበረክቱት። ነገር ግን አሁን ጥሩ ለውጦች እየመጡ ነው። ይሄ ደሞ ማሳያው የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት መልበሻ ክፍል ድረስ እየመጡ አይዟችሁ በርቱ ይሉን ነበር። ይሄ ደሞ ለኛ ትልቅ ነገር ነው። በአጠቃላይ ዝግጅት ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ጥሩ ድጋፎች ተደርገውልን ነበረ” ሲል ስለ አቀባበሉ እና ስለተደረገላቸው ድጋፍ ተመስገን ተናግሯል።

ስለ ውድድሩ በቀጣይ ማብራሪያ የሰጠው አሰልጣኙ “ውድድሩ በጣም አሪፍ ነበር። ቡድናችን በጣም ተፎካካሪ እና ጠንካራ እንደነበረ ሁሉም ሰው ታዝቧል። በኮኮብነት ፉክክሩ ላይ ሁለት ተጨዋቾች ከኛ ቡድን አሸንፈው ተሸላሚ መሆናቸው ችለዋል። ይህ ደሞ የሚያሳየው ምን ያህል ጠንካራ እና ጎበዝ ልጆች እንዳሉን ነው። ውድድሩ ላይ የተሳተፉት ሌሎች ሃገራት ይዘዋቸው የመጡት ተጨዋቾች እድሜያቸው በጣም የሚያጠራጥር ነው ትላንት የገጠምነውን ዩጋንዳን ጨምሮ ይህ ደግሞ ውድድሩ ሙሉ ለሙሉ የጠራ ውድድር ነው ብሎ ለማመን ይቸግራል”ብሏል።

በቀጣይ ለአፍሪካ ዋንጫው እንዳናልፍ ያደረጉን ምክንያቶች ብሎ የሚያስባቸውን ጉዳዮች የዘረዘረው አሰልጣኝ ተመስገን በተለይ የልምድ ማነስ ተጨዋቾቹን እንደጎዳቸው ያስረዳል። “አብዛኛው ውድድሩ ላይ የነበሩት ቡድኖች ከዚህ በፊት ብሩንዲ ላይ ይዘዋቸው የነበሩ ተጨዋቾችን ነው ይዘው አሁን የቀረቡት። እኛ ግን ብሩንዲ ላይ ከነበረው የቡድን ስብስብ አንድ ተጨዋች ብቻ ነው አሁን የያዝነው። እሱንም በዛ ሰዓት ሶስተኛ ተጠባባቂ የነበረውን ግብ ጠባቂ፤ ስለዚህ ሁሉም የውድድር እና የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ልምድ አልባ ነበሩ። ይሄ ደሞ ዋነኛ ግባችንን እንዳናሳካ ያደረገን ምክንያት ነው” ብሏል።

ተመስገን ጨምሮም ስለ ቡድኑ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ማብሪያራ የሰጠ ሲሆን የቡድኑ ህብረት እዚህ ደረጃ እንዳደረሳቸው ይናገራል” ቡድናችን በጣም የሚገርም ህብረት ነበረው። ብዙ ችግሮችን የምንፈታው በመነጋገር ነው ይሄ ደሞ ነገሮች ቀለል እንዲሉልን አድርጓል። ደካማ ጎናችን ደግሞ የተለመደው የአየር ላይ እና የቆሙ ኳሶችን የምንከላከልበት መንገድ ነው። ይህ ችግር ደግሞ በእኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በዋናውም ብሄራዊ ብድን በክለቦችም ደረጃ የአፍሪካ ሃገራት እና ክለቦችን ስንገጥም የምንቸገርበት ነገር ነው። እኛም ደሞ በዚህ ነገር  እንደምንቸገር ቀድሞ ገብቶን ነበረ ነገር ግን ይህንን ችግር ለመቅረፍ ተደጋጋሚ የሜዳ ላይ ስራዎች እና ልምምዶች አላደረግንም ይህ የሆነው ደሞ ከነበረን አጭር ጊዜ አንፃር ነው እዚህ እያለን ስድስት ትሬዲንጎችን ብቻ ነው የሰራነው በስድስት ልምምድ ደሞ እነዚህን ችግሮች ልትቀርፍ አትችልም ያለን አማራች ለልጆቹ ነገሮችን እንዲያከናውኑ በቃል መንገር ብቻ ነው” ብሏል።

በመቀጠል ከትላንቱ ሽንፈት በኃላ ቡድኑ ላይ ስለተፈጠረው መንፈስ ይህን ብሏል። “እውነት ለመናገር ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ አንድ እግራችንን አስገብተን አንደኛውን ልናስገባ ስንል በመውደቃችን በጣም አዝነናል። ትላንትም ተጨዋቾቹ ላይ የመረበሽ እና የመደናገጥ ነገር ከጨዋታው በኃላ አይቼ ነበረ ነገር ግን ምንም ማለት እንዳልሆነ በማስረዳት ከዛ ስሜት እንዲወጡ ስራዎችን ሰርተናል።” ብለው ከጨዋታው በኃላ ታንዛኒያ የሚገኙ አትዮጵያዊያኖች ከጎናችን ሆነው ሲደግፉን እና ሲያበረታቱን እንዲሁም ከትላንቱ የፍፃሜ ጨዋታ በኃላ የእራት ግብዣ አድርገው አይዟችሁ ማለታቸው ተጨዋቾቹ ቶሎ ከስሜታቸው እንዲወጡ እንደረዳቸው ጨምረው አስረድተዋል።

በመጨረሻም የሱ ቀጣይ ቆይታ እና ቡድኑ ላይ መደረግ ስላለበት ነገሮች ተመስገን ምላሽ ሰጥቷል። ” እኔ የሶስት ወር ኮንትራት ብቻ ነው የተሰጠኝ እሱም እያለቀ ነው ወደፊት የሚመጣውን እና የሚከሰተውን ነገር አላቅም፤ ግን ልጆቹ ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋሉ። ቡድናችን ውስጥ ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች አሉ እነሱን ደግሞ ተንከባክበን ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ አለብን። ብዙ ጊዜ በሃገራችን የግብ ጠባቂ እና የአጥቂ ችግር አለ ተብሎ ይነገራል ነገር ግን በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የኛ ግብ ጠባቂ እና አጥቂ በኮከብነት ተሸልመው መጥተዋል። ይህ ደግሞ የሚያሳየው እንደሚባለው የግብ ጠባቂም የአጥቂም ችግር እንደሌለብን ነገር ግን እንዳልሰራን ነው። ከተሰራ አሁንም ብዙ እንደነሱ አይነቶችን ማውጣት እንደምንችል ነው።” ብለው ተጨዋቾቹ እንደ ከዚህ ቀደሙ የታዳጊ ቡድኖች ተረስተው እንዳይቀሩ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።