ለቀይ ቀበሮዎቹ ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች የማበረታቻ ሽልማት ተበረከተ

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች በዛሬው እለት ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ የማበረታቻ ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል። 

በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድኑ በታንዛንያ አስተናጋጅነት ሲከናወን በነበረው የሴካፋ ዞን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር ለፍፃሜ ደርሶ በዩጋንዳ 3ለ1 ተሸንፎ ለአፍሪካ ዋንጫው ሳይልፍ መቅረቱ ይታወሳል። ከ15 ቀን የታንዛንያ ቆይታ በኃላ ዛሬ ማለዳ ወደ አዲስ አበባ የገባው ብሄራዊ ቡድኑ ረፋድ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የእንኳን ደና መጣችሁ አቀባበል የተደረገ ሲሆን ምሽት 10:30 ደግሞ በብሉ ስካይ ሆቴል የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በቦታው የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራን ጨምሮ ሌሎች የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የተገኙ ሲሆን ከሽልማት አሰጣት ስነ ስርዓቱ በፊት በተለያዩ ግለሰቦች ንግግሮች አድርገዋል።

በዝግጅቱ መክፈቻ እና መዝጊያ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ በተመዘገበው ውጤት በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል። ” በተመዘገበው ውጤት ደስተኞች ነን። ይህ ውድድር ምን ያህል ቁጭቶች እንደፈጠረባችሁ ታዝቢያለው። ይሄ የቁጭት ስሜት ደግሞ ለወደፊት አላማችሁ በጣም ይጠቅማችኋል። አሁን ብዙም ስራዎች ስላልተሰሩ ከዚህ በላይ ውጤት እንዲመጣ አንጠብቅም። ወደፊት ግን በነባር አሰራር አንቀጥልም፣ ተስፋ እንዳላችሁ አይተናል፤ በወጥነት ታዳጊ ብሄራዊ ቡድኖችን ተከታታይ ስልጠናዎችን እና ተገቢ ክትትል እንዲሰጣቸው እናደርጋለን።” በማለት ፌዴሬሽኑ ትልቅ የቤት ስራ በታዳጊዎች ላይ እንደሚጠብቀው ገልፀዋል።

በመቀጠል የማበረታቻ ሽልማት ለተጨዋቾቹ እና ለአሰልጣኝ ቡድን አባላቶቹ የተሰጠ ሲሆን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ተመስገን ዳና፣ ምክትል አሰልጣኙ ደረጄ ተስፋዬ፣ የቡድን መሪው ደረሰ እንዲሁም የህክምና ባለሙያው በቀለ ተስፋዬ እያንዳንዳቸው 10ሺ ብር ተሸልመዋል። በተጨማሪም የቡድኑ ሁሉም ተጨዋቾች እያንዳንዳቸው 5ሺ ብር ተበርክቶላቸዋል።
ከሽልማቱ በኃላ የቡድኑ አሰልጣኞች እና ተጨዋቾች ሃሳባቸውን የገለፁ ሲሆን በተለይ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ስለተደረጋቸው ነገር እና ስለተሰጣቸው ድጋፍ ፌደሬሽኑን አመስግኗል።

ከተመስገን እና ከተጨዋቾቹ ንግግር በኃላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ለብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች መልክት አስተላልፈዋል። “በመጀመሪያ ያመጣችሁት ውጤት ሊያስመሰግነችሁ ይገባል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በትክክለኛ እድሜ ተጉዞ እንደዚህ አይነት ውጤት ያመጣ የመጀመሪያው ተብላችሁ በታሪክ እንደምትወደሱ ልመሰክርላችሁ እወዳለው።” ብለው ሃሳባቸውን የቀጠሉት አቶ ሰውነት ” እናንተ እና የእናንተ መሰል ታዳጊዎች ከዚህ በኃላ ለ20 ዓመት በታቹ ብሄራዊ ቡድን ግብዓቶች ናችሁ። ስለዚህ ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ ለዚህ ለመብቃት ጠንክራችሁ ልትሰሩ ይገባል” በማለት ለተጨዋቾቹ የቤት ስራ የሚሰጥ ንግግር አድርገው ዝግጅቱ ተጠናቋል።