የከፍተኛ ሊጉ የዋንጫና የመለያ ጨዋታዎች ቀን እና ቦታ ላይ ለውጥ ተደረገ 

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በከፍተኛ ሊግ የዋንጫ እና ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማለፍ የሚደረገው የመለያ ጨዋታ ላይ የቀን እና የቦታ ለውጥ ለማድረግ መወሰኑ ታውቋል።

ሁለቱ ጨዋታዎች ከዚህ ቀደም ነሀሴ 26 እና 27 በድሬዳዋ እንዲደረጉ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ለውጥ ተደርጓል። የድሬዳዋ ስታድየም በአሁኑ ወቅት በእድሳት ላይ የሚገኝ በመሆኑና ለጨዋታዎቹ ብቁ ስለማይሆን ለቦታ ለውጡ ምክንያት እንደሆነ ተሰምቷል።

በለውጡ መሰረት በሽረ እንዳስላሴ እና ጅማ አባ ቡና መካከል ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚደረገው የመለያ ጨዋታ ማክሰኞ ነሀሴ 29 ቀን 2010 ሀዋሳ ላይ ሲካሄድ በባህር ዳር ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ መካከል የሚደረገው የዋንጫ ጨዋታ ቀን በተመሳሳይ ማክሰኞ ነሀሴ 29 አዳማ አበበ ቢቂላ ጨዋታው የሚደረግበት ሜዳ እንደሆነ ታውቋል። ጨዋታዎቹ ሀዋሳ እና አዳማ የሆኑበት ምክንያትም ለሁሉም ቡድኖች ገለልተኛ በመሆናቸው ነው ተብሏል።

የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ ወሳኝ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት ተካሂደው ደቡብ ፖሊስ አንደኛ፣ ጅማ አበ ቡና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው የሚታወስ ነው።