ሀገር አቀፍ የታዳጊዎች ስልጠና ምዘና ውድድር ዛሬ ተጠናቀቀ

ከነሀሴ 13 ጀምሮ በአዳማ ሲካሄድ የሰነበተው የሀገር አቀፍ የታዳጊዎች ስልጠና ምዘና ውድድር የእግርኳስ ዘርፍ ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል።

በወንዶች ለፍፃሜ የደረሱት ኦሮሚያ እና አማራ ናቸው። በግማሽ ፍፃሜው ሀረሪ በመለያ ምቶች አማራን ማሸነፍ ቢችልም ከጨዋታው በፊት የተጫዋች ተገቢነት ክስ አስይዘው የነበሩት አማራዎች በፎርፌ አሸናፊ እንዲሆኑ ሲደረግ ኦሮሚያ ደግሞ ደቡብን 6-3 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ነው ወደ ፍፃሜ ያመራው። 

አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ በተከናወነው በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያው ደቂቃ ላይ የአማራ ቡድን አበበ አሳምነው ባስቆጠረው ግብ ቢመራም ከ7ደቂቃዎች በኋላ በተሾመ በላቸው ጎል አቻ የሆኑት ኦሮሚያዎች በ25ኛው ደቂቃ አድናን ረሻድ እና በ39ኛው ደቂቃ ቶላወቅ ተስፋዬ ባስቆጠሯቸው ተጨማሪ ሁለት ጎሎች 3-1 በመምራት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል። ከዕረፍት መልስ ተጨማሪ ግብ ለማስተናገድ  30 ደቂቃ ያህል የፈጀ ሲሆን አማራ ከመሸነፍ ያልዳነበትን ጎል በናትናኤር ማስረሻ አማካኝነት አግኝቶ ጨዋታውም በኦሮሚያ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከፍፃሜው በፊት ለደረጃ ሊደረግ የነበረው የሐረሪ እና ደቡብ ጨዋታ ሐረሪ በጨዋታ ስፍራ ላይ ባለመገኘቱ በፎርፌ የደቡብ ቡድን የሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል።

05:00 ላይ በተደረገው የሴቶች የፍፃሜ ጨዋታ ደቡብ ክልል አዲስ አበባን 3-1 በማሸፍ የአምና ክብሩን አስጠብቋል። ለደቡብ ያይናለም ዓለምዬ ሁለት፣ ዳግማዊት ሰለሞን አንድ ሲያስቆጥሩ ለአዲስ አበባ የምርትኪዳን ተካልኝ አስቆጥራለች።

በ3:00 ሰዓት ላይ ለደረጃ በተደረገው ጨዋታ አማራ ኦሮሚያን 1-0 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል።