የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ መታሰብያ የታዳጊዎች ውድድር ቅዳሜ ይጠናቀቃል

በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር አዘጋጅነት ለክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያነት የሚካሄደው ውድድር ለፍፃሜ የደረሱ ክለቦች ታውቀዋል።

ለ13ኛ ተከታታይ ዓመት ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማን ለመዘከር በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበት አዘጋጅነት የሚዘጋጀው የታዳጊዎች ውድድር ከሐምሌ 30 ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

በውድድሩ ቀድሞ 122 ቡድኖች ከአዲስ አበባ እና ክልል ከተሞች ቀድመው እንደተመዘገቡ መገለፁ የሚታወስ ሲሆን ለውድድሩ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ብቁ የሆኑትን 88 ክለቦች በመለየት እንደተጀመረ ይታወቃል።

በዶን ቦስኮ ካቶሊክ ትምህርት ቤት ሜዳ እየተካሄደ በሚገኘው ውድድር የዙር እና የምድብ ከዛም የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ሲካሄዱ ቆይተው ትላንት የፍፃሜ ግማሽ ጨዋታዎች ተከናውነዋል።

በግማሽ ፍፃሜው ጨዋታ የነገ ተስፋ መካኒሳን 1ለ0 እንዲሁም ድል አንለያይምን በመለያ ምት 7ለ6 በመርታት ለፍፃሜ መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።

ይህን ተከትሎ የፊታችን ቅዳሜ ጳግሜ 3 የፍፃሜ እና የደረጃ ጨዋታዎች እንደሚደረጉ ታውቋል። ለደረጃ መካኒሳ ከአንለያይም ለዋንጫ ደግሞ የነገ ተስፋ ከድል እንደሚጫወቱ መርሃ ግብር እንደወጣላቸው ክለቡ በይፋዊ ገፁ አስታውቋል።

የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የመታሰቢያ ውድድር ላለፉት 12 ዓመታት ሲዘጋጅ ክለቡ በርካታ ታዳጊዎችን ለራሱ እና ለሌሎች ክለቦች ማውጣት ችሏል።